በጌዴኦ ዞን ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬትና የይዞታ ማረጋገጫ ሥራ እየተፋጠነ ነው

93
ዲላ ህዳር 1/2011 በጌዴኦ ዞን ተጓትቶ የቆየውን ሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬትና ይዞታ ማረጋገጫ ሥራ ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገለጸ፡፡ መምሪያው ለመሬት ልኬት ቀያሽና ምዝገባ ባለሙያዎች የክህሎት ክፍተት ማሟያ ሥልጠና በወናጎ ወረዳ እየሰጠ ነው፡፡ በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጋሞ እንደገለፁት በዞኑ የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬትና የይዞታ ማረጋገጫ ሥራ በ2004 ዓ.ም ቢጀመርም እስካሁን አልተጠናቀቀም ፡፡ እንደ አቶ ከበደ ገለጻ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ማነስ፣ በዞንና በወረዳዎች ለስራው አነስተኛ በጀት መመደብ እንዲሁም የባለሙያዎች ክህሎት ክፍተት ለሥራው መጓተት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ፡፡ መምሪያው ሥራውን ለማፋጠን ከዞን አስተዳደር ባገኘው በጀት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ከወረዳ ባለሙያዎች በተጨማሪ በራሱ ቀያሽና መዝጋቢ ባለሙያዎችን በኮንትራት በመቅጠር ከ50 ሺህ 800 በላይ የመሬት ልኬትና ምዝገባ ማከናወኑን ነው የገለጹት። ይህም ልኬትና ምዝገባ የተካሄደባቸውን መሬቶች ቁጥር ወደ 174 ሺህ 789 ከፍ ማድረጉን አስረድተዋል። አቶ ከበደ እንዳሉት በዞኑ ካሉ 133 የገጠር ቀበሌዎች 109ኙ ልኬት የተጀመረባቸው ሲሆኑ በ40 ቀበሌዎች የልኬትና ምዝገባ ሥራ ተጠናቋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ልኬት ሥራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስለሚሰራ የባለሙያውን እውቀትና ክህሎት ማዳበር ወሳኝ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመው ስልጠናው ከዚህ በፊት የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ የመሬት ልኬቱ አርሶ አደሩ ከክርክር ነፃ የሆነ የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖረው ከማድረጉም ባሻገር መሬቱን በዋስትና አስይዞ ለመጠቀም እንደሚያስችለው ገልጸዋል። ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የቅየሳ ባለሙያ የሆነው በሀይሉ ጠቀቦ ከዚህ በፊት ሥልጠና ሳያገኝ ወደሥራ መግባቱን ገለጾ በእዚህም  ጥራት ያለው ልኬት ለማከናወን ብዙ ጊዜ ይወሰድበት እንደነበር ተናግሯል ፡፡ ሥልጠናው በርካታ ክፍተቶቹን እንደሚሞላለት የገለፀው ባለሙያው በተለይ ለአርሶ አደሩ ጥራት ያለው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰርቶ ለማስረከብ እንደሚያስችለው ጠቁሟል ፡፡ ለሥራው የሚያስፈልጉ ዘመናዊ መሳሪያዎች አጠቃቀም ክፍተት እንደነበረባት የገለጸችው ሌላዋ የቅየሳ ባለሙያ መስታወት ግዛቸው በበኩሏ  ከስልጠናው የምታገኘው እውቀት አቅሟን እንደሚያሳድግላት ተናግራለች ፡፡ በወናጎ ወረዳ ሱጋሌ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ክፍሌ ጋኒ በበኩላቸው ያላቸው መሬት ተለክቶ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታና ደብተር እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ እንደአርሶ አደሩ ገለጻ ከዚህ በፊት ዘመናዊ የመሬት ልኬትና ካርታ ባለመኖሩ የቡና ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት እሳቸውን ጨምሮ በአካባቢያቸው በርካታ አርሶ አደሮች በይገባኛል ተጋጭተው ጊዜያቸውን በክስ ሂደት ሲያጠፉ ቆይተዋል፡፡ "በአሁኑ ወቅት ማሳዬን ማንም የኔ ነው ብሎ እንዳይከራከረኝ የይዞታ ማረጋገጫ አለኝ" ያሉት አርሶ አደር ክፍሌ ካርታቸውን በዋስትና በማስያዝ ከገንዘብ ተቋማት ብድር ለመውሰድ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንድ ሄክታር የመሬት ይዞታ እንዳላቸው የገለጹት ሴት አርሶ አደር ታየች ንጉሴ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ሴቶች የይዞታ ባለቤትነት መብት እንዳልነበራቸው ገልፀዋል ፡፡ "አሁን የባለቤትነት መብታችን ተረጋግጦልናል" ያሉት አርሶ አደሯ በስማቸው ያለውን መሬት እንሰትና ቡና በማምረት በመጠቀም ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል ፡፡ በወናጎ ወረዳ እየተሰጠ ባለው ስልጠና 77 ቀያሽና መዝጋቢ ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም