በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ስጋት ለግጭት ምክንያት እየሆነ ነው-ምሁራን

126
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 በኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ስጋት የግጭት መንስኤ እየሆነ መምጣቱን ምሁራን ተናገሩ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተፈጠሩ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ጉዳት እየደረሰ ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨሲርቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳሬይክተር ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ለኢዜአ ሲናገሩ ኢትዮጵያ በትክልል ከተጠቀመችበት ለሁሉም ዜጎች የሚበቃ ሀብት አላት። ይህንን ሀብት በአግባቡና ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መጠቀም አለመቻል በተለያዩ ቦታዎች "ተጠቃሚ አልሆንኩም" በሚል የግጭት ምክንያት ሆኗል ይላሉ። የሀብት ተደራሽነት ስጋት ወጣቱን ለስደትና ለግጭት እየዳረገው መሆኑን በመግለጽ ይህም የኢኮኖሚ ጥያቄ መሆኑን በምክንያትነት ያቀርባሉ። በኢትዮጵያ ሁሉም ህዝብ በማንኛውም ቦታ እኩል መብት ያለው ቢሆንም ይህን ለማጣጣም ጊዜ እየፈጀብን ነው ብለዋል። የፌዴራል አካሄዱ በቋንቋና ብሄር ላይ የተመሰረተ መሆኑ የራሱ ችግር እንዳለው በመግለጽም "ይህን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው" የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ የህዝብ የምክክር መድረክ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን "ጎሳና አካባቢን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ድርጅት አንድ የግጭት መንስኤ በመሆኑ መፍትሄ ሊኖረው ይገባል" በማለት የጋራ አቋም አስፈላጊ መሆኑንም ያሰምሩበታል። የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን እንደሚሉት ህዝቡ መንግስት በሰጠው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተጠቅሞ ሃሳቡን በተለያየ መንገድ እየገለጸ ይገኛል። ሆኖም "ግጭት ሲኖር መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ይሰጣል" የሚል አስተሳሰብ ሌላ ግጭት እየወለደ በመሆኑ በአጭሩ ሊቋጭ እንደሚገባው በማንሳት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ። መሰል ግጭቶች በሽግግር ጊዜ የሚከሰቱ በመሆናቸውና በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው ይህ በመሆኑ በቅርቡ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር ከመንግስትና ከህዝቡ ጋር በመሆን ሰዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹና ሰላማቸውንም በዚያው ልክ እንዲጠብቁ ያደርጋል የሚል እምነት አላቸው። የግጭት መነሻው በርካታ ቢሆንም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር፤ ክልል የመሆንና ራስን የማስተዳደር ጥያቄ፤ ሌሎች ከአካባቢያችን ይውጡ እኛ ብቻ ተጠቃሚ እንሁን የሚሉት ምክንያቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም