በኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች ተቀባይነት መቀነስ አሳሳቢ ሆኗል

369
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 በኢትዮጵያ ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች ተቀባይነታቸው እየቀነሰ መምጣት እንዳሳሰባቸው የኃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ተናገሩ። ሰሞኑን በድሬዳዋ አስተዳደር የአምስቱ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የተውጣጡ ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ሰላምን እያደፈረሱ ባሉ ጉዳዮችና መፍትሄዎቻቸው ላይ መክረዋል። በዚህ ጊዜ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች፤ አባገዳዎች፤ የአገር ሽማግሌዎችና  ምሁራን በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ትታወቅበት የነበረው ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች በአዲሱ ትውልድ ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም። ይህ የግጭት አፈታት ዘዴ እንደየአካባቢው ባህልና ልምድ ይለያይ እንጂ ጥፋተኛው የሚቀጣበትና ለወደፊቱ የሚታረምበት እንዲሁም ሰላም ማውረድ አላማውን አንድ እንደሚያደርገው አስተያየት ሰጪዎች ያነሳሉ። ሊቀብርሃናት ቀለምወርቅ ቢምረው በአንድ ወቅት በመሳሪያ ሊጋደሉ የነበሩ ሰዎችን በኃይማኖት ስርዓት ማስቆማቸውን በማስታወስ በአሁኑ ወቅት ይህ አይነት ስርዓት በህዝቡ ዘንድ እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራሉ። አባገዳ ሙሳ አሊ በህዝቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር በዳይና ተበዳይም በአንድ ላይ ተቀምጠው በግልጽ ችግሮቻቸውን ተነጋግረው ፍትህ እንደሚሰጥ የገዳ ስርዓትን ግጭት አፈታት ያስረዳሉ።። በአሁኑ ወቅት ግን የግጭቱ አይነት ፖለቲካዊ ይዘት እየያዘ መምጣቱ በገዳ ስርዓት መዳኘት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ነው የሚናገሩት። በተለይም ወጣቶች የግጭት ተሳታፊ እየሆኑና ለግጭት አፈታት ስርዓቱም ተገዥነታቸው አነስተኛ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል። በመኢሶ ወረዳ የአገር ሽማግሌ የሆኑት በድሩ አህመድ እንደሚሉት በአካባቢያቸው ሰዎች በግጦሽ መሬትም ሆነ በሌሎች ሲጋጩ የአገር ሽማግሌዎች የጠቡን ምክንያት ለማወቅ ቁጭ ብለው ይወያያሉ። ከዚያም ጥፋተኛውን ጠርተው ለምን ችግሩን እንደፈጠረ ተጠይቆ ጥፋቱን ሲያምን እንደ ጥፋቱ ክብደትና ቅለት ቅጣት ይተላለፍበታል። ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ይህ ባህላዊ የችግር መፍቻ ስርዓት ተቀባይነት እያጣ በመምጣቱ ጥፋተኞችን በሚያጋልጡ ሰዎች ላይም እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ችግሮችን እየፈታች የመጣችው በባህላዊ ችግር መፍቻ እሴቶች መሆኑን የሚናገሩት የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች ህብረት አስተባባሪ ኢንጂነር ጌታሁን ሁሴን ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ለነዚህ ባህላዊ እሴቶች መንግስት ትኩረት አለመስጠቱ ዋጋ እያስከፈለው በመሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ባህላዊ ግጭት አፈታት ዘዴ በመንግስት አልፈታ ያለውን ግጭት ጨምሮ በባህላዊ የግጭት አፈታት ግጭቶችን መፍታት ከአባቶቻቸው የወረሱት ስርዓት ነበር። ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶች እንደየአካባቢው መጠሪያቸው የተለያየ ሲሆን ለአብነትም በኦሮሞ ጃርሱማ፣ በአማራ ሸንጎ፣ በሃድያ አራረዎ ይጠቀሳሉ። ነገር ግን እነዚህ ዘላቂ ሰላም የሚፈጥሩ አገረ-ሰባዊ የዳኝነት ስርዓቶች አሁን አሁን ችላ እየተባሉ መምጣታቸው አሳሳቢ መሆኑንና ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ምሁራን ይመክራሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም