ዕድሜያቸው አንድ ዓመት ከ3 ወር ለሞላቸው ህጻናት ሁለተኛ ዙር የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ሊሰጥ ነው

101
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 ዕድሜያቸው አንድ ዓመት ከ3 ወር ለሞላቸው ህጻናት ከህዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሁለተኛ ዙር የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል። ክትባቱ በሁሉም ጤና ኬላዎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብር መስጠት እንደሚጀምር ያስታወቀው ጤና ሚኒስቴር ነው። በኢትዮጵያ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በመደበኛው የክትባት አገልግሎት ህጻናት ዘጠኝ ወር ሲሞላቸው ይሰጣል፤ አሁን የሚሰጠውና አዲሱ ሁለተኛ ዙር መደበኛ ክትባት የህጻናቱን የኩፍኝ መከላከል አቅም ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ተነግሯል። የኩፍኝ ክትባትን አንድ ጊዜ በመከተብ በሽታውን 85 በመቶ መከላከል የሚቻል ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ማለትም ህፃናቱ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ሲሆናቸው የሚከተቡት ደግሞ የመከላከል አቅምን ከ99 በመቶ በላይ ያደርሰዋል። ኩፍኝ በዓለም ላይ ለህጻናት ህመም፣ የአካል ጉዳትና ሞት ምክንያት ከሆኑ ዋና ዋና በሽታዎች አንዱ ነው። በሽታው የኩፍኝ ቫይረስ በሚባል ረቂቅ ተህዋስያን የሚከሰትና በንክኪና በትንፋሽ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ይዛመታል። ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ህጻናት በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች በሽታው ቀላሉ ሊዛመት ይችላል። ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከራስ ፀጉር ጀምሮ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች የሚዛመት ሽፍታ፣ የአይን መደፍረስ ወይም መቅላት፣ ከአፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ መብዛት፣ የዓይን እንባ ማዘልና ሳል የበሽታው ምልክቶች ናቸው። በጤና ሚኒስቴር የክትባቱ አስተባባሪ ዶክተር ተክላይ ኪዳኔ በሽታውን በዋናነት መከላከል የሚቻለው 'ህጻናትን በማስከተብ ብቻ ነው' ይላሉ። በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከመጪው ህዳር ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁለተኛውን ዙር የኩፍኝ ክትባት ለህፃናት በመደበኛነት ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል። በዓለም ላይ ባለፉት 16 ዓመታት 20 ሚሊዮን ዜጎችን የኩፍኝ ክትባት በመከተብ ከሞት መታደግ መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም