በ200 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሜዲካል ጋዝ ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

56
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውና በ200 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሜዲካል ጋዝ ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከል ተመረቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ያስገነባውን ማዕከል የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ዛሬ መርቀውታል። የሜዲካል ጋዝ /ኦከስጂን/ ምርቱን ህሙማን መኝታ ክፍል የሚገኙ አልጋዎች ድረስ የሚያደርሱ መስመሮችም ተዘርግተዋል። ማዕከሉ የጋዝ ሲሊንደሮችን ህሙማን መኝታ ክፍል ለማድረስ የሚያስፈልገውን የሰው ጉልበት፣ በሆስፒታሎች መሰረተ ልማቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳትና ሌሎች ችግሮች ያስቀራል። የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በአገሪቷ በሚገኙ ሆስፒታሎች ተመሳሳይ ማዕከሎችን የማስፋፋት ስራዎች እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ለ10 ሆስፒታሎች የሜዲካል ጋዝ ማምረቻና ማከፋፈያ ማዕከላትን እያንዳንቸውን በ200 ሚሊዮን ብር መገንባት ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም 411 ሆስፒታሎች በደረጃ ሁለትና ሶስት የሚዳረሱ ይሆናል ብለዋል። የኮሌጁ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛኸኝ በበኩላቸው የማዕከሉ መገንባት በወጪም ሆነ በኦክሲጅን ጥራት ላይ የነበሩ ችግሮችን እንደሚያቃልል ተናግረዋል። የኦክስጂን ማዕከሉ ለህሙማን የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶችን በተቀናጀና ምቹ በሆነ ሁኔታ መስጠት እንደሚያስችልም አክለዋል። ኮሌጁ ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠቀም ጥራት ያለው የህክምና ተቋም ለመሆንና የህክምና መንደር ለመመስረት ከያዛቸው እቅዶች መካከል ማዕከል አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል። የሜዲካል ጋዝ ማምረቻ ማዕከሉ ለሌሎች የጤና ተቋማት በሲሊንደር እየሞላ ለሽያጭ የሚያቀርብ ሲሆን በየቀኑ 100 ሲሊንደሮችን የመሙላት አቅም አለው። የኃይል መቆራረጥ የሜዲካል ጋዝ የማምረት ስራውን እንዳያስተጓጉለውም ለማዕከሉ ሁለት ጄኔሬተሮች ተተክለውለታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም