የትግራይ አርሶ አደሮች ወቅቱን ያልጠበቀውን ዝናብ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን ለማምረት ሊጠቀሙበት ይገባል

72
መቀሌ  ጥቅምት 30/2011 አርሶ አደሮች ወቅቱን ሳይጠብቅ እየጣለ ያለውን ዝናብ  ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን ለማምረት እንዲጠቀሙበት የትግራይ  የክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አሳሰበ። የክልሉ አርሶ አደሮች እየጣለ ባለው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይደናገጡ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንዳለባቸው ተገልጿል። የትግራይ የክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ ለኢዜአ እንደገለጹት የክልሉ አርሶ አደሮች ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት ወቅቱን ሳይጠብቅ እየጣለ ያለውን ዝናብ መጠቀም ይገባቸዋል፡፡ "የክልሉ አርሶ አደሮች በዝናቡ የሚመጣ ጉዳት ፈርተው መዘናጋት አይገባቸውም" ያሉት ኃላፊው፣ የደረሱ ሰብሎቻቸውን በማንሳት ቶሎ በሚደርሱ ጥራጥሬዎች መተካት አለባቸው ብለዋል። በክልሉ እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እስከሚቀጥለው ወር ድረስ ስለሚቀጥል ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ  ደጋፊ እንዲሆን በማሰብም መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ምክራቸውን አስተላልፈዋል። የዝናብ ስርጭቱ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልና ለእንስሳት ቀለብ፣ለመስኖ ልማትና ለከርሰ ምድር ውሃ መጎልበት አስተዋጽኦ በሚኖረው መልኩ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ዝናቡን ጥቅም ላይ ለማዋልም የግብርና ባለሙያዎች ተሰማርተው ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን ዶክተር አትንኩት አስታውቀዋል። የክልሉ አርሶ አደሮች የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክርና ድጋፍ ተቀብለው እየጣለ ባለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሳይደናገጡ  ሰብላቸውን ተጋግዘውና ተባብረው መሰብሰብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በየአከባቢው የሚገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ተማሪዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች አርሶ አደሮችን በማገዝ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል። በትግራይ ክልል  በ2010/11 የምርት ዘመን በሰብል ከተሸፈነው ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም