ቅዱስ ጊዮርጊስ ስቴዋርት ጆን ሀልን አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ

60
አዲስ አበባ ጥቅምት 30/2011 ብሪታኒያዊው ስቴዋርት ጆን ሀል አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ። አሰልጣኙ በይፋ ዛሬ ስራቸውን እንደሚጀምሩና ትናንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ ዋና ጸሀፊ፣ የቡድን መሪ እና የአሰልጣኝ አባላት ጋር ትውውቅ ማድረጋቸውን ከክለቡ የስፖርት ማህበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አሰልጣኙ የቆይታ ጊዜና ከውሉ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማህበሩ በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። የ62 ዓመቱ ስቴዋርት ጆን ሆል ፖርቹጋላዊውን ማኑኤል ቫዝ ፒንቶንን በመተካት ነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ የሆኑት። አሰልጣኙ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከመረከባቸው በፊት የባንግላዴሽን ሳይፍ ስፖርት ክለብን ያሰለጥኑ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው ናቸው። ስቴዋርት የህንዱን ፑኔ፣ የታንዛንያውን አዛም፣ የኬንያውን ኤኤፍሲ ሊኦፓርድና ሶፋፓካ ክለቦችን አሰልጥነዋል። በተጨማሪም የዛንዚባርና የሴይንት ቪሰንት እና ግሬናዲያስ (Saint Vincent and the Grenadines) ዋና እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን አሰልጥነዋል። አሰልጣኙ በቀደመው ጊዜ የበርሚንግሃም ሲቲ እግር ኳስ አካዳሚ ዳይሬክተር እና የተተኪ ቡድኑ እና ከ18 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝም ነበሩ። የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በ83 ዓመት ታሪኩ የውጭ አገር አሰልጣኞችን የመቅጠር ባህል አለው። ብራዚላዊው ኔይደር ዶስ ሳንቶስ፣ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ሬኔ ፌለር፣ ጀርመናዊ ሚሼል ክሩገር፣ ሰርቢያዊው ሚሉቴን ሰርዶቪች ሙሉቲን “ሚቾ”፣ ሆላንዳዊው ሀንስ ቫንደር ፕሊዩም፣ ኢጣልያዊያኑ ጂዮሴፔ ዶሴና ፒዬር ሉዊጂ ዳንኤሎና ሆላንዳዊው ማርት ኖይና ፖርቹጋላዊው ማኑኤል ቫዝ ፒንቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚህ በፊት ያሰለጠኑ የውጭ አገር አሰልጣኞች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም