የምርጥ ዘር እጥረትን ለማቃለል እየሰራ መሆኑን በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ

101
ጎባ ጥቅምት 30/2011 በአርሶ አደሩ ዘንድ የሚታየውን የምርጥ ዘር እጥረት ለማቃለል ከ9 ሺህ 800 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ምርጥ ዘር እያባዛ መሆኑን በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የሥራ ግምገማና ግብረ መልስ አስተባባሪ አቶ መልካሙ ጌታቸው እንዳስታወቁት 2010 /2011 ምርት ዘመን እየተባዙ ከሚገኙት ምርጥ ዘር መካከል የዳቦና የፓስታ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላና በቆሎ ይግኙበታል። እነዚህ ዝርያዎች የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከልን ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጪ ከሚገኙ የምርምር ማዕከላት የተለቀቁና በሄከታር በአማካይ ከ45 እስከ 60 ኩንታል ምርት የመስጠት አቅም እንዳላቸው አስታውቀዋል። በአርሶ አደሩ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸውን “ቀቀባ”፣ “ሆጎልቾ” እና “ፓቫኒ” የተሰኙ የዳቦና ማካሮኒ ስንዴ ዝርያዎችን ከ5 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በማባዛት ተጠቃሚውን ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም አቶ መልካሙ ጠቅሰዋል። በአጠቃላይ በምርጥ ዘር ከተሸፈነው መሬት ከ306 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኘል ተብሎ እንደሚጠበቅ በቅርቡ በተደረገው የቅድመ ምርት ግምገማ መረጋገጡንም ነው የገለጹት። እንደ  አስተባባሪው ገለጻ ኢንተርፕራይዙ ዓምና ካባዛው ምርጥ ዘር ውስጥ ለዘንድሮው መኽር እርሻ አገልግሎት እንዲውል 95 ሺህ 271 ኩንታል የተለያየ ምርጥ ዘር ለዞኑ አርሶ አደሮች አሰራጭቷል፡፡ ኢንተርፕራይዙ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ ያለው በምርምር የወጡ መስራች ዝርያዎችን ከምርምር ተቋማት ተቀብሎ በራሱ እርሻ ላይ በማባዛትና አዋጭነታቸውን በመገምገም ጭምር መሆኑንም አስረድተዋል። ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ አርሶ አደር ሁሴን ኡስማን በሰጡት አስተያየት “ከዚህ በፊት የአካባቢውን ዝርያ ሲጠቀሙ ከአንድ ሄክታር መሬት ያገኙት የነበረው ከ15 ኩንታል የስንዴ ምርት አይበልጥም ነበር። ከኢንተርፕራይዙ ያገኙትን ምርጥ ዝርያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ በሄክታር ከአራት እጥፍ በላይ በማሳደግ እስከ 65 ኩንታል ስንዴ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተመጣጣኝ ዋጋ ከኢንተርፕራይዙ የሚቀርብላቸውን ምርጥ ዘር መጠቀም ከጀመሩ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው አርሶ አደር መሐመድ ኢብራሂም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢንተርፕራይዙ ያገኙትን “መዳ ወላቡ” የሚባል ስያሜ የተሰጠውን የስንዴ ዝርያ በሁለት ሄክታር ማሳቸው ላይ ሙሉ የግብርና ፓኬጅ ተጠቅመው እያለሙ መሆናቸውንና ከአምና የተሻላ ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል። በኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ቅርንጫፍ በዞኑ የሚገኙ ሮቤና ሲናና እርሻዎችን ጨምሮ በምስራቅ አርሲ ዞን ሄራሮ፣ ሁንጤና ቢሊቶ ስራሮ በሚባሉ አካባቢዎች 15 ሺህ 846 ሄክታር መሬት እንደሚያስተዳድር ለማወቅ ተችላል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም