የጋምቤላ ከተማ እድገት የሚፋጠንበት መዋቅራዊ መሪ ፕላን እየተዘጋጀ ነው

79
ጋምቤላ ጥቅምት 30/2011 የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን እድገት የሚያፋጥንበት መዋቅራዊ መሪ ፕላን በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገለጸ። አስተዳደሩ አዲስ እየተዘጋጀ ባለው ፕላን  ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር ትናንት ተወያይቷል። ከንቲባው አቶ ቺቢ ቺቢ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በከተማዋ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና እድገቷንም ለማፋጠን የሚያስችል ፕላን እየተዘጋጀ ነው። ፕላኑ በተለይም የከተማውን የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮች ለማቃለልና የጎርፍ ተጠቂነቷን ይቀንሳል ብለዋል። በተጨማሪም በከተማው የሚታየውን ሕገ ወጥ የመሬት ወረራና በግለሰቦችም ሆነ በድርጅቶች ተይዞ ወደ ልማት ያልገባ መሬትን ለማልማት እንደሚያስችል ተናግረዋል። በተለይም ከተማዋን በ2020 የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ከንቲባው፣ ለፕላኑ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። በአሁኑ ወቅት የፕላኑ ጥናት ተጠናቆ የማስተካከያና ተጨማሪ ግብዓቶችን በመሰባሰብ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ቺቢ አስረድተዋል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የጋምቤላ ከተማ መዋቅራዊ መሪ ፕላን ጥናት አስተባባሪ አቶ ሞላ ዓይንአበባ እንደተናገሩት ፕላኑ በከተማዋ በዋናነት የሚታየውን የመሠረተ ልማት ችግር ይፈታል። እድገቷንም ያፋጥናል። በተለይም ከተማዋን ለሁለት ከፍሏት የሚያልፈው የባሮ ወንዝ ለከተማዋ ውበትና እድገት ተጨማሪ አቅም ስለሚፈጥር ፕላኑ ወንዙን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ፕላኑ ከተማዋ ዘመናዊ የአከታተም ሥርዓት ኖሯት የመሬት ሀብቷን ጥቅም ላይ በማዋል ፈጣን እድገት ለማምጣት ያስችላታል ብለዋል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ በከን ኡጁሉ በሰጡት አስተያየት ፕላኑ ወደ ተግባር ከተለወጠ የከተማዋን ገጽታ በአጭር ጊዜ ለመቀየር ያስችላል ብለዋል። አስተዳደሩ ለፕላኑ ተግባራዊነት ጠንክሮ እንዲሰራ አስተያየት ሰጪው ጠይቀዋል። በከተማው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመስፋፋቱ የትራፊክ መጨናነቅ እየተፈጠረ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኡሞድ ኡሜት ናቸው። በመሆኑም ፕላኑ ''በከተማው የቀለበት መንገድን ጨምሮ ሌሎች መንገዶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱ ህዝቡ በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው'' ብለዋል። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ፕላን ለ10 ዓመታት እንደሚያገለግል ከከተማው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም