በመቀሌ ከተማ የ11 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ሥራ ሊከናወን ነው

980

መቀሌ ጥቅምት 30/2011 በመቀሌ ከተማ ከ77 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የ11 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የከተማው ኮንስትራክሽንና መንገድ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዓለም ሀዱሽ ለኢዜአ እንደገለጹት በተያዘው ዓመት ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በከተማው በአምስት ክፍለ ከተሞች 11 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ በድንጋይ ንጣፍ ይሰራል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በድንጋይ ንጣፍ ሥራ የሚሰማሩ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች ተመልምለውና በማህበር ተደራጅተው ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ በየከፍለ ከተማው የሚሰሩ መንገዶችን የመምረጥና የመንገድ ቅየሳ ሥራው አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ መደረጉን ነው ኃላፊው ያስረዳው፡፡

አቶ ተስፋዓለም እንዳሉት በ35 የልማት ቡድኖች ተደራጅተው ስልጠና እየወሰዱ ያሉ ወጣቶች በህዳር ወር አጋማሽ ሥራ ይጀምራሉ፡፡

የሚነጠፈው ድንጋይ ጥራት ያለውና ረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችል በጥርብ ድንጋይ የተደረጁ ስድስት የልማት ቡድኖች የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል፡፡

ይህም ባለፉት ዓመታት የድንጋይ ንጣፍ መንገድ በዘፈቀደ እየተሰራ ይፈጠር የነበረው የጥራት ችግርና የጊዜ መጓተትን እንደሚያስቀርም ተናግረዋል፡፡

እንደአቶ ተስፋዓለም ገለጻ ባለፈው ዓመት ከደላላ ጋር በመመሳጠር ቀርቦ የነበረ 26 መኪና ጥራቱን ያልጠበቀ ድንጋይ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን ተደርጓል።

በመንገድ ግንባታ ሥራው ለመሰማራት ስልጠና በመከታተል ላይ ከሚገኙ ማህበራት መካከል የህዳሴ ወጣቶች ልማት ቡድን አስተባባሪ ወጣት መሰረት ታደሰ እንደገለጸው ስልጠናው በየክፍለ ከተማው መሆኑ በአግባቡ ስልጠናውን ለመከታተል ጠቀሜታ አለው።

” ለስልጠና ከአካባቢያችን ርቀን ስንሄድ እናወጣው የነበረውን የትራንስፖርትና የመግብ ወጪም ታድጎናል ” ብሏል፡፡

መንግስት ህብረተሰቡን አደራጅቶ ወደሥራ ለማስገባት እያደረገ ያለው ጥረት በተለይ ወጣቶች ከማሳተፍ ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ስለሚያረጋግጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቋል።

“በድንጋይ ንጣፍ ሥራ ተሰማርተን የምናገኘውን ገቢ ቀጣይ በማህበር ለመስራት ለምናቅደው ሥራ መነሻ ካፒታል” ይሆናል ያለው ደግሞ የመሰቦ ወጣቶች ልማት ቡድን አስተባባሪ ወጣት ገብረእግዚአብሔር ተካ ነው፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት በመቀሌ በመቀሌ ከተማ 167 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ መሰራቱን ከቢሮው የተገኘውን መረጃ ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።