አዲስ አበባ 13ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓልን በልዩ ዝግጅት ለማክበር እየተዘጋጀች ነው

2259

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011  አዲስ አበባ 13ኛውን የብሄር ብሄረሰቦች ክብረ በዓል ከሌላው ጊዜ በተለየ ድምቀትና መንፈስ ለማክበር ዝግጅት እያደረገች ነው።

ከክብረ በዓሉ ክዋኔዎች መካከል ከ10 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሚታደሙበት የቡና ማፍላትና መጠጣት ስነ-ስርዓት ይገኝበታል።

የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን “በብዝኃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2011 በአገሪቱ ርእሰ መዲና ነው የሚከበረው።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ሰሎሞን ኪዳኔን ጨምሮ የክልል ምክር ቤቶች አፈጉባኤዎች፣ የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የኮሙኒኬሽን ቢሮዎች ኃላፊዎች በተገኙበት በክብረ በዓሉ ዝግጅት ላይ ያተኮረ ምክክር ዛሬ ተካሂዷል።

የዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ነስረዲን መሐመድ በዚሁ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ የዘንድሮውን በዓል ከቀደሙት በተለየ መልኩ አንድነትን በሚያጎሉና አሳታፊ በሆኑ ልዩ ልዩ ኩነቶች ለማክበር መታቀዱን ገልጸዋል።

ሰብሳቢው እንዳሉት “የኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ የእኔም ነው” በሚል መንፈስ ክልሎች ከራሳቸው ክልል በተጨማሪ የሌሎች ክልሎችን አለባበስ፣ አጨፋፈርና የባህል ክዋኔዎችን የሚያቀርቡበት መሆኑ የዘንድሮውን በዓል ለየት ያደርገዋል።

በዚህም መሰረት አንደኛው ክልል የሌላኛውን ብሄረሰብ ትርኢት ለማቅረብ ስምምነት ላይ በመደረሱ  “ማን የማንን ባህልና ወግ ወክሎ ትርኢት ማቅረብ አለበት” የሚለው በዕጣ ተለይቷል።

“አንዱ የሌላውን ክልል ባህል እንዲያቀርብ መደረጉ ሁሉም የሌላውን ባህል በመለማመድ በኢትዮጵያ ያለው ልዩ ልዩ ባህልና ክዋኔ የራሱም ጭምር መሆኑን እንዲቀበል፤ ይህንንም ተከትሎ የ”ኢትዮጵያዊነት” ስሜት አይሎ እንዲወጣ ለማድረግ ያግዛል” ብለዋል።

ሰብሳቢው እንዳሉት በዚህ ትርኢት ላይ ከየክልሉ አንድ ሴትና ወንድ ታዳጊዎች የተካተቱ መሆኑ ክብረ በዓሉ ከሌላው ጊዜ በተለየ ታዳጊዎች ላይ የአንድነትና ኢትዮጵያዊ ስሜት ለማስረፅ ያግዛል።

ከየክልሉ የሚመረጡት እነዚህ ህፃናት ከበዓሉ አስቀድመው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሁለቱን ቤተመንግስቶች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና መሰል ተቋማትን የሚጎበኙ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም ይወያያሉ።

“ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ” በሚል የቡና ማፍላትና መጠጣት ስነ-ስርዓት የሚዘጋጅ ሲሆን በዚህም ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚታደሙ ተናግረዋል።

የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የቡና አፈላል ክዋኔ የሚከተለው ይህ የቡና ማፍላትና መጠጣት ስነ-ስርዓቱ የኢትዮጵያን ቡና ለማስተዋወቅ እንደሚረዳም ገልፀዋል።

በቡና ማፍላት ስነ-ስርዓቱ ላየ የሚሳተፈው ህዝብ ብዛት ከፍተኛነት ምናልባትም የመጀመሪያው ሊሆን እንደሚችል ነው አቶ ነስረዲን የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ “የዘንድሮው በዓል አከባበር ቀድሞ ከተከናወኑት ክፍተቶች ትምህርት ተወስዶበት ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በስፋት የሚያጎሉ ተግባራት የሚንፀባረቁበት ይሆናል” ብለዋል።

ከበዓሉ በኋላም  እየታየ ያለውን ክልላዊ አስተሳሰብ በአገራዊ አስተሳሰብ ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ መርሃ-ግብሮቹን የተሳኩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሲምፖዚየሞችና ውይቶች፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር፣ ከጎዮርጊስ ቤተ-ክርስያን ብሄራዊ ቴአትር የሚደረግ የአደባባይ ትርኢት የዘንድሮው ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል አካል መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በሚዘጋጁ የጥናት ፅሁፎች ላይም የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል።

በእለቱ በስታዲየም በሚኖረው የበዓል አከባበር ከ30 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል።