ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን የተመለከተውን የውሳኔ ሀሳብ ነገ ያጽድቃል ተብሎ ይጠበቃል

154
አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ በሚያካሂደው ልዩ ስብሰባ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን የተመለከተውን የውሳኔ ሀሳብ ያጽድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ባደረገው ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ሳያጸድቅ መቅረቱ የሚታወስ ነው። በነገው ስብስባ የምክር ቤቱ አባላት ቀጣይ ውይይት አድርጎ የውሳኔ ሀሳቡን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ማክሰኞ ምክር ቤቱ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ሀሳቡ ሌላ ጊዜ ቀርቦ እንዲጸድቅ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት የአመራር ምደባው የትምህርት ዝግጅትን፣ ልምድንና የአመራር ብቃትን ታሳቢ ያደረገ መሆን ነበረበት ብለዋል። በተለይ ሊቃነ-መናብርቱ የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴና የትምህርት ዝግጅታቸው አብሮ መሄድ ነበረበት ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል። ከዚህ በፊት በቸልተኝነት አጀንዳዎች ሲወሰኑ ዝም ብለው ሲመለከቱ የነበሩ አባላት በምደባው ተካተዋል፤ ይሄ አግባብ አይደለም ያሉ ሲሆን በዚህም "ፓርላማው ጥርስ የለውም" ሲባል ነበር፤ ከዚህ በኋላ የቀረበልንን ሁሉ ማጽደቅ የለብንም፤ መጽደቅ የሌለበት ነገር መጽደቅ የለበትም የሚል ሀሳብ በማምጣት የሞገቱም  ነበሩ። በአንጻሩ ሌሎች የምክር ቤት አባላት ደግሞ በአገሪቷ ውስጥ ለውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት "ልክ እንደ ደሴት ለውጥ አያስፈለገንም የሚል አቋም መያዝ ተገቢ አይደለም" ሲሉም ተደምጠዋል። የውሳኔ ሀሳቡን በማጽደቅ የአፈጻጸም ችግሮች ካሉ ወደፊት እያዩ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይሻሻል ያሉ የምክር ቤት አባላት ደግሞ "ጊዜው ከመሄዱ አኳያ ቶሎ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባት አለበት" በሚል ተከራክረዋል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የአመራር ምደባው በተቻለ መጠን የትምህርት ዝግጅትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ጥረት መደረጉን አብራርተዋል። ''የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀትም ሆነ የአመራር ምደባው ቋሚ አይደለም፤ በአፈጻጸም እየተገመገመ ሊቀየር የሚችልበት ዕድል ይኖራል'' ሲሉም ነው ያብራሩት። የምክር ቤቱ አባላት በውሳኔ ሀሳቡ ላይ በሰፊው ከተከራከሩ በኋላ የአመራርና የአባላት ምደባው የውሳኔ ሀሳብ በይደር እንዲተላለፍ ተወስኗል። ምክር ቤቱ በስድስተኛ መደበኛ ስብሰባው ያሉትን የቋሚ ኮሚቴዎች ቁጥር ወደ አስር ዝቅ እንዲል ውሳኔ ማሰለፉ ይታወቃል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን የሥራ ስንብት በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ባደረገው ስብሰባ እንደ ቋሚ ኮሚቴው ሁሉ የዳኛ ስንብቱን የውሳኔ ሀሳቡ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም