በድረ-ገጽ የተላለፈ መረጃ በካፋ ዞን የህዝብ ቁጣ አስነሳ

71
ሚዛን ጥቅምት 29/2011 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን "ዓለም አቀፍ የቡና ቱሪዝም ቀን" በካፋ ዞን እንደሚካሔድ በድረ-ገጹ ካሳወቀ በኋላ ከሁለት ቀናት በፊት መረጃውን በመቀየሩ የአካባቢውን ህዝብ አስቆጥቷል። ትናትን መንገድ በመዝጋት የተጀመረው የአካባቢው ህብረተሰብ ተቃውሞ ዛሬ በሰላማዊ ሰልፍ ቀጥሎ ውሏል፡፡ በሰልፉ ላይ የተገኙት አቶ አበበ አስፋው የተባሉ የከተማው ነዋሪ የካፋ የቡና መገኛነትና የባለቤትነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ከፍተኛ ቅራኔ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ "ካፋ የቡና መገኛ ስለመሆኑ በታሪክ የሚወሳና የሚታወቅ ቢሆንም ከሰሞኑ ከባለስልጣኑ የተለቀቀው መረጃ በህዝቡ ውስጥ ቅሬታ ፈጥሯል" ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት የካፋ ቡና ታሪካዊነቱን በማረጋገጥ ለሕብረተሰቡ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ነው የገለጹት። አቶ ደረጄ መኮንን የተባሉ ሌላኛው የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ በበኩላቸው "በግሌ የሰማሁት ነገር ግራ የሚያጋባና ታሪክ የሚያፋልስ ነው" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ "መንግስት ለህዝቡ ይፋ በሚያደርጋቸው ታሪካዊ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባልም" ሲሉም ጠቁመዋል። አቶ ደረጄ እንዳሉት ህዝቡ ባካሄደው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ያለምንም የፀጥታ ችግር ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። "በከተማው ብሔራዊ የቡና ሙዚየሙ ተገንብቶ ለረዥም ዓመታት አገለግሎት ሳይሰጥ መቆየቱ በህዝብ ላይ ጥያቄ ሲፈጥር ቆይቶ ዳግም ይሄ መከሰቱ የሚያሳዝን ነው" ያሉት ደግሞ አቶ መሃመድ ይመር የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው፡፡ መንግስት ጉዳዩን በማጤን አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ "ህዝቡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን እንዳቀረበ ሁሉ መንግስትም ለህዝቡ ተገቢና ፈጣን ምላሽ መስጠት አለበት" ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ በሰልፉ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው "ባለስልጣኑ በመጀመሪያ ዓለም አቀፍ የቡና ቱሪዝም ቀን የቡና መገኛ በሆነችው ካፋ እንደሚከበር በድረ-ገጹ ገልጾ ከሁለት ቀን በፊት የቡና መገኛ በሆነችው ጅማ እንደሚከበር መግለጹ በህዝብ ዘንድ ተቃውሞ አስነስቷል" ብለዋል። ካፋ የቡና መገኛ መሆኑ ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም በሚል በህብረተሰቡ ዘንድ ቅራኔ መፍጠሩን ገልጸው፣ በዚህም ህብረተሰቡ ከትናንት ጀምሮ መንገድ በመዝጋትና በተለያየ መልክ ተቃውሞውን ሲገልጽ መቆየቱን ተናግረዋል፡ ችግሩን ለመፍታት በአሁኑ ወቀት የዞኑ መንግስት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ እየመከረ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ "ህብረተሰቡ ያለውን ተቃውሞና ቅሬታ በሰውና በንብረት ላይ ምንም ጉዳት ሳያስከትል በመገልጹ ሊመሰገን ይገባል" ሲሉም አቶ ማስረሻ ገልጸዋል። ከትናንት ጀምሮ ቦንጋን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያገናኝ የትራንስፖርት መንገድ፣ የአካባቢው የንግድ እቅስቃሴና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መቆማቸው ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም