ዶክተር ወርቅነህ የኤርትራ አምባሳደርን የሹመት ደብዳቤ ቅጂ ተቀበሉ

56
አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደርን የሹመት ደብዳቤ ቅጂ ተቀበሉ። ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር ሰመረ ርዕሶምን የሹመት ደብዳቤ ቅጂ በመቀበል በሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ  ግንኙነት ዙሪያ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ዶክተር ወርቅነህ በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው የሰላም ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉንና ግንኙነቱን ለማሳደግ በሁለቱም ወገን እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው አምባሳደሩ በቆይታቸው ለዚህ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው እምነታቸውን ገልጸዋል። ዶክተር ወርቅነህ በድንበር ንግድና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር ረገድ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ሚኒስትሩ አያይዘውም በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ የተደረገው ጥረት ወደሚፈለገው አቅጣጫ እያመራ መሆኑ እንዳስደሰታቸውና ኢትዮጵያ ስታደርግ የቆየችውን ከፍተኛ ጥረት እስከፍጻሜው አጠናክራ እንደምትቀጥል አስረድተዋል። አምባሳደር ሰመረ ርዕሶም በበኩላቸው በቆይታቸው የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጠንክረው እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም