በልማትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ስብሰባ በአላማጣ ከተማ እየተካሄደ ነው

65
ማይጨው ጥቅምት 29/2011 በትግራይ ደቡባዊ ዞን በሚካሄዱ የልማት ሥራዎችና የተለያዩ  ጉዳዮች ላይ የሚመክር የአንድ ቀን ስብሰባ በአላማጣ ከተማ መካሄድ ጀመረ። በስብሰባው ላይ በትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራና የክልሉ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎችን ያካተት ቡድን ተገኝቷል። ዶክተር ደብረጽዮን ስብሰባውን በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት የውይይቱ ዓላማ በክልሉ በ2011 ዓ.ም ለማከናወን በታቀዱ ዝርዝር የልማት ሥራዎች ላይ ከህብረተሰቡ ጋር በመወያያት የማሻሻያ ሐሳቦችን መቀበል ነው። ከእዚህ በተጨማሪ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ህዝብ ያሉበትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥባቸው ማድረግ የውይይቱ ሌላው ዓላማ መሆኑን ዶክተር ደብረፅዮን አመልክተዋል። በስብሰባው ላይ ከትግራይ ደቡባዊ ዞን ስምንት ወረዳዎች የተውጣጡ ከ300 በላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል። ከስብሰባው በኋላ በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው የክልሉ ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ቡድን በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም