ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተዋል

73
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ለመካፈል ዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ አምርተዋል። ጉባዔው በዋናነት የአፍሪካ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም የአገራቱን የልማት ውጥኖች ለማሳካት በሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ምክክር ያደርጋል ተብሏል። በጉባኤው ላይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ተያያዥነት ያላቸው አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንቷ በቆይታቸው ከደቡብ አፍሪካ መሪዎች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል እና ተሞክሮ ታስተዋውቃለች ተብሎ እንደሚጠበቅም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በፎረሙ በአፍሪካ የሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ባለሃብቶች እንደሚታደሙም ተገልጿል። የጆሃንስበርጉ ጉዞ ፕሬዝዳንቷ ከተሾሙ በኋላ ወደ ውጭ አገር የሚያደርጉት ሁለተኛው ነው። በመስከረም ወር 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተፈረመውን የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ለማብሰር በተዘጋጀው ስነስርዓት ላይ  ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ባለፈው ሳምንት ጁባ ተገኝተው በስነ ስርዓቱ ላይ መታደማቸው የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም