በመንገድ ልማትና በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ

70
ሚዛን ጥቅምት 28/2011 በመንገድ ልማትና በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ችግሮች የመልካም አስተዳደር ምንጭ በመሆናቸው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡ የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የ2010 አፈጻጸምና የቀጣይ ዕቅድ ላይ የሚመክር ጉባዔ ትናንት በሚዛን አማን ከተማ ማካሄድ ጀምሯል፡፡ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንዳሉት መንግስት በከፍተኛ በጀት ከሚያከናውናቸው ልማት አውታሮች አንዱ የመንገድ መሰረተ ልማት ነው፡፡ መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም በሚታየው የአፈጻጸም ውስንነት የሚጠበቀውን ውጤት ማሰካት አልተቻለም፡፡ በክልሉ ለበርካታ ዓመታት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ የመንገድ ግንባታዎች መኖራቸውን በማሳያነት የጠቀሱት አቶ አብርሃም ይህም የህዝብ ቅሬታ ምንጭ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በተያዘው በጀት አመት የታቀዱ የመደበኛ መንገድ ግንባታና የጥገና ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወኑ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ያሉትን የመናኻሪያ አገልግሎቶች ከማጠናከር ባለፈ የተገልጋዩን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ አዳዲስ መናኸሪያዎችን መክፈት  እንደሚገባም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የቤንች ማጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ዘማች በዛብህ በበኩላቸው የመንገድ መሠረተ ልማት የዞኑ ቀዳሚ የመልካም አስተዳደር ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ፣ በጥራትና በተለያዩ ምክንያት አገልግሎት ያቆሙ የመንገድ ሥራዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ''የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች መስፋፋት ለውጥን በማሳለጥ የሚኖራቸው ሚና የጎላ በመሆኑ በቀጣይ የህዝቡን ፍላጎት ለመመለስ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ዘርፎች አንዱ ይሆናል'' ብለዋል፡፡ ከጉባዔው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወርቅነህ አገኘው እንዳሉት የትራፊክ አደጋ ለሰው ህይወት ህልፈትና ለንብረት ውድመት ምክንያት በመሆኑ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የትራንፖርት ስምሪትና ቁጥጥር ላይ የሚታዩ መሰረታዊ ችግሮችን በመለየት መፍታት እንደሚገባ አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡ መድረኩ ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን  የዞንና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ባሙያዎችና ሃላፊዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም