ትውልደ ሶማሊያዊና ፍልስጤማዊ ሴቶች የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ሆነው ተመረጡ

99
ጥቅምት28/2011 ከእርስ በእርስ ጦርነት ሽሽት ወደ አሜሪካ የተሰደደችው ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኢልሃን ኦማር እና በስደት አሜሪካ ከገቡ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች በሚሺጋን ግዛት የተወለደችው ረሺዳ ትላቢብ የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ሆነው ተመርጠዋል። ኢልሃን ኦማር እና ረሺዳ ትላቢብ ሁለቱም የዴሞክራት ተወካይ ሲሆኑ እነሱን ጨምሮ በርካታ የአናሳ ማህበረሰብ ተወካይ ተመራጮች የማሸነፍ እድል ማግኘታቸው ነው የተነገረው። በሚኔሶታ የምትኖረው የ36 ዓመቷ ትውልደ ሶማሊዊቷ ኢልሃን ኦማር የግዛቱ ተወካይ ስትሆን በኮንግረሱ ተወካይ የነበሩትን ኬት ኤሊሶንን ትተካለች ተብሎ ይጠበቃል። ኤልሃን ኦማር በዴሞክራት ፓርቲ የሚቀነቀኑትን ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎት ሽፋን፣ የትምህርት ክፍያ ማስቀረትን የቤት ልማት መርሃ ግብር የመሳሰሉ ፖሊሲዎችን በምርጫ ንቅናቄዋ ስታራምደ ነበር ተብሏል። ትውልደ ሶማሊያዊቷ የህጻንነት ዘመኗን የመጀመሪያ አራት ዓመታት በኬንያ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ ነው ያሳለፈችው። በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ታሪክ ኢልሃን ኦማር የመጀመሪያዋ ሙስሊም መሆኗን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የ42 ዓመቷ ፍልስጤም-አሜሪካዊቷ ትላቢብ በፈረንጆቹ 2008 የሚሺጋን ግዛት የህግ አውጭ ምክር ቤት አባልነት ያሸነፈች የመጀመሪያዋ ሙስሊም ናት። የህክምና አገልግሎት ለሁሉም የሚለው መርሃ ግብረ አቀንቃኝ በስደተኞች ዙሪያ ያሉ ፖሊሲዎች እንዲቃኙ ሀሳብ በማመንጨት ትታወቃለች። የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማቀንቀን የምትታወቀው ትላቢብ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እርምጃዎች ከሚተቹት ተርታ ትመደባለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም