በምእራብ ሸዋ ዞን በኮትቻ መሬት ላይ የለማውን ሰብል በመሰብሰብ ዳግም የማልማት ስራ እየተካሄደ ነው

72
አምቦ ጥቅምት 28/2011 በምእራብ ሸዋ ዞን ባለፈው የመኸር ወቅት የኮትቻ አፈርን በማጠንፈፍ 23 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የለማውን ሰብል በመሰብሰብ ዳግም የማልማት ስራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በልማቱ የተሳተፉ የዞኑ አርሶአደሮች ጥቁር አፈርን በዘመናዊ መንገድ በማጠንፈፍ በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የአፈር ልማት ማሻሻያ ቡድን ባለሙያ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ቀቀባ እንዳሉት   በክረምት ወቅት 22 ሺህ 969 ሄክታር በዘመናዊ መንገድ በማጠንፈፍ በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል፡፡ በዘጠኝ ወረዳዎች ጥቁር አፈርን በዘመናዊ መንገድ በማጠንፈፍ ከለማው ከዚሁ ማሳ 689 ሺ 675 ኩንታል በላይ የተለያየ የሰብል ምርት ይጠበቃል፡፡ በማንጣፈፍ ስራው ከ2 ሺህ በላይ ሴቶች የሚገኙበት 26 ሺህ 714 አርሶ አደሮች ያለሙትን የሰብል ምርት በአሁኑ ወቅት እየሰበሰቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ለሥራው ውጤታማነት 876 ዘመናዊ ማረሻዎች ተሰራጭተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጉን አስረድተዋል። ባለሙያዋ እንዳሉት “አይ ባር ቢቢ ኤም”  በሚል የሚጠራው የተሻሻለ ማረሻ  በማሳ ላይ የሚተኛውን ውሃ በማጠንፈፍ  ለልማቱ  ውጤታማነት  ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ነው። በኮትቻ አፈር ልማቱ አጠቃላይ ከለማው መሬትም በአማካኝ በሄክታር 39 ኩንታል ምርት እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በኮትቻ አፈር የእርሻ ማሳ ላይ የተኛውን ውሃ በዘመናዊና ባህላዊ ዘዴ በማጠንፈፍ አርሶአደሩ በመኽር ወቅት ያለማውን ሰብል በመሰብሰብም ቀሪ ዕርጥበትን በመጠቀም መሬቱን በሌሎች ሰብሎች ዳግም የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዳግም ልማቱ እስካሁን ከ14 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በምስር፣ በጓያና ሽንብራ ሰብሎች መልማቱን ጠቅሳው 259 ሺ 200 ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተበሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም የአርሶ አደሮችን ተሞክሮ በማስፋት በዞኑ ኖኖ፣ ሚዳቀኝና ጀልዱ ወረዳዎች በጥናት የተለየውን አንድ ሺ 582 ሄክታር የኮትቻ መሬት በማልማት የዞኑን ምርታማነት ለመጨመር እየተሰራ መሆኑንም ወይዘሮ አለምጸሃይ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ በጥቁር አፈር ልማት ስራው የተሰማሩ የደንዲ ወረዳ አርሶአደር ለታ ድርርሳ ቴክኖሎጂው በዓመት ሁለት ጊዜ የተለያዩ ሰብሎችን ማልማት ከማስቻሉ በላይ ምርታቸው በመጨመሩ በኑሮአቸው ላይ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአደአ በርጋ አርሶአደር ፍቃዱ ጅሬኛ በሰጡት አስተያየት ጥቁር አፈርን በዘመናዊ መንገድ በማጠንፈፍ በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ከዚህ በፊት ከጥቁር አፈር መሬት በሄክታር 10 ኩንታል ስንዴ ያገኙ እንደነበር የገለፁት አስተያየት ሰጪው በአሁኑ ወቅት ''በቴክኖሎጂ ታግዘው በማልማት እስከ 36 ኩንታል እያገኘሁ ነው'' ብለዋል፡፡ በጥቁር አፈር ልማት መሰማራት ከጀመሩ ወዲህ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ምርት በማግኘታቸው በኑሮአቸው ለውጥ መምጣቱን ያመለከቱት ደግሞ የሜታ ሮቢ ወረዳ አርሶአደር አቶ  ድርባ ጉርሜሳ ናቸው፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም