በደረቅ ወደብ አገልግሎት አሰጣጥ የሚታየውን ችግር ለመፍታት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ተባለ

112
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሚሰጠው አገልግሎት  የሚታየውን ችግር ለማስወገድ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ጠየቀ። በትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እና በገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ የሞጆ ደረቅ ወደብ የእቃ ማስተናገጃን (ተርሚናልን) ጎብኝቷል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት ወሳኝ ነው። የወጪና ገቢ እቃዎች እንቅስቃሴ ቀልጣፋና ውጤታማ ካልሆነ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል ያሉት ሚኒስትሯ በተርሚናሉ የሚታዩ የአሰራር ጉድለቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ስራ ላይ በማዋል በአሁኑ ወቅት በሞጆ ደረቅ ወደብ ያለውን የኮንቴይነር ቆይታ ከ47 ቀን ወደ 2 ቀን ዝቅ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል። በተርሚናሉ ያለውን የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መስሪያ ቤቱ የተጠናከረ ድጋፍ ያደርጋል  ነው ያሉት  ወይዘሮ ዳግማዊት። የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት በሞጆ ደረቅ ወደብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ችግር ለማስወገድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደገፈ አሰራር በመከተልና ያለውን የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በኩል የውሳኔ አሰጣጥን በቁርጠኝነት ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሞጆ ደረቅ ወደብ የተከማቹ ኮንቴነሮች አራት ቢሊዮን ብር ይዘው የተቀመጡ ናቸው። ባለሀብቶች ያስመጧቸውን ኮንቴነሮች እንዲያነሱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ቢሰራም በቂ ምላሽ እየተገኘ አይደለምም ብለዋል። ''የግል ድርጅቶችም ሆኑ የመንግስት ተቋማት በወደቡ ያከማቹትን ኮንቴነሮች በአፋጣኝ የማንሳት ግዴታ አለባቸው'' ሲሉም ተናግረዋል። ወደቡ በአንድ ጊዜ ከ14 ሺህ 9 መቶ በላይ ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ብቻ ከ13 ሺህ በላይ ኮንቴነሮች ወደብ ላይ ይገኛሉ ብለዋል። በአገሪቱ ከፍተኛ የምግብ ዘይት ፍላጎት ያለ ቢሆንም አስመጪዎች ከሁለት ወር በላይ ያስቆጠሩ 3 ሺህ 856 የምግብ ዘይት የያዙ ኮንቴነሮች በወደቡ እንደሚገኙም አቶ ሮባ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ከሁለት ወር በላይ የቆዩ 234 የመንግስት ተቋማት ኮንቴነሮች በወደቡ ተከማችተው ይገኛሉ ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከእነዚህ መካከል የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ 111፣ የትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ 91 ኮንቴነሮች ይጠቀሳሉ ብለዋል። እንደ አቶ ሮባ ገለጻ ኮንቴነሮቹ በጊዜ ባለመነሳታቸው በመንግስት ገቢ አሰባሰብ፣ በደረቅ ወደብ አገልግሎት እና በመጋዘን ኪራይ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው። በኢትዮጵያ ካሉት 7 የደረቅ ወደቦች ውስጥ የሞጆ ደረቅ ወደብ ተርሚናል 78 በመቶ የገቢና የወጪ ንግድ አገልግሎት የሚከናወንበት ትልቁ ወደብ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም