ለተጀመረው ለውጥ መሳካት የድርሻችንን እንወጣለን---የድሬዳዋ የሃገር ሽማግሌዎች

84
ድሬዳዋ ጥቅምት 27/2011 የተጀመረውን ለውጥ ዳር ለማድረስና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ከተማ ኡጋዞች፣አባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ገለጹ። ቀደም ሲል በከተማው ባጋጠመ ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ የማቋቋም ስራው በዚህ ሳምንት እንደሚጀመር የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል። የሃገር ሽማግሌዎቹ ከከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ጋር ትላንት ባደረጉት ውይይት ላይ እንደገለጹት በሶማሌና በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ለህግ ለማቅረብ ይሰራሉ። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አባገዳ አብዱልማሊክ ዩኑስ እንደተናገሩት ወጣቶች ከስሜት በመውጣት የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ መስራት አለባቨው ብለዋል፡፡ “በየደረጃው የሚገኘው ነዋሪም ለሰላም መከበርና ለልማት መረጋገጥ የድርሻቸውን ሊወጣ ይገባል’’ብለዋል። የግጭት ቀስቃሾች የድሬዳዋን መለወጥና ልማት የማይፈልጉ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የኢሳ ማህበረሰብ ባህላዊ መሪ ኡጋዝ ሙስጠፌ መሃመድ ናቸው። ህብረተሰቡ በተለይ ቄሮዎች በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላትን ለፍትህ በማቅረብ ዘላቂ ሰላም ማስከበርና በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ከዳር ማድረስ እንደሚገባቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል። የሀገር ሽማግሌው መሃመድ አህመድ ጮሬ የኦሮሚያና የሶማሌ ወንድማማች ህዝቦችን የዘመናት አብሮነት  የሚያለያይ አንዳችም ምክንያት እንደሌለ ተናግረዋል። “በተለይ በአሁኑ ጊዜ አካባቢያችንን በራሳችን ልጆች እያስተዳደርን ነው፤ይህን ታላቅ ሃላፊነት መጠበቅና በሀገር የተጀመረውን ለውጥ ማሳካት ይገባል’’ብለዋል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ባስተላለፉት መልዕክት ጥቅማቸው የተነካባቸውን አካላት በየጊዜው ሰላምን ለማደፍረስ የሚያደርጉት ጥረት በተቀናጀ መንገድ በቁጥጥር ስር እየዋለ ይገኛል። በሁከትና ረብሻ የተሳተፉ አካላትን ለህግ የማቅረቡ ስራ እንደሚጠናከር ተናግረው ህብረተሰቡም ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ከፍትህ አካላት ጋር በመጣመር ሊሰራ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የሀገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዞችና አባገዳዎቹ ሀምሌ 29/2010 ዓ.ም በገንደ ገራዳ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው በመመለስ በኩል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። በገንደገራዳና ለገሀሬ አካባቢ ያለውን ሰላም አስተማማኝ በማድረግ ዳግም ችግር እንዳይፈጠር እንደሚሰሩም ለከንቲባው አረጋግጠዋል። በጽህፈት ቤታቸው ውይይቱን የመሩት ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን እንዳሉት ኡጋዞችና አባገዳዎች እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች አቋም ለከተማ አስተዳደሩ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ትልቅ አቅም ነው። ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው የመመለሱ ስራ በዚህ ሳምንት እንደሚጀምርም ጠቁመዋል። በመሆኑም በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ በየተሰማራበትና ባለበት ስፍራ ሰላምን በማስጠበቅና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ በማድረግ በኩል ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ ላይ በከተማው የሚገኙ የሃገር ሽማግሌዎች ኡጋዞች አባገዳዎችና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ የከተማው የጸጥታ ኃላፊዎችም ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም