የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ለልማት መረጋገጥ እየሰራ ነው-አፈ ጉባዔ አብዱልሰላም

826

ድሬዳዋ ጥቅምት 27/2011 የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር  ለዘላቂ ሰላም መስፈንና ለልማት ማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አፈ ጉባዔው አስታወቁ።

በቋሚ ኮሚቴዎች የተጓደሉ አባላት ተመርጠዋል።

አፈ-ጉባዔው አቶ  አብዱልሰላም መሐመድ የአስተዳደሩ ምክር ቤት 40ኛ መደበኛ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት በአስተዳደሩ ዘላቂ ሰላምን እንዲሰፍንንና ልማትን ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ነው።

የምክር ቤቱ አባላት በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ከዳር ለማድረስ እየተከናወኑ ያሉትን ተግባራትን በማጠናከርም ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታትና የግጭት መንስዔዎችን አስቀድመው ለመከላከል በኅብረተሰቡ ውስጥ  የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ ተገተው እንዲንቀሳቀሱም አስገንዝበዋል።

በተለይ ከተማዋ የምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል መጻኢ ተስፋን የሚያሳኩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እውን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት ለሰላም ተገቢውን ዋጋ መስጠት ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለሁለት ቀናት የቆየው ጉባዔ በተለያዩ ምክንያቶች የተጓደሉ አምስት የቋሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።

በዚህም ወይዘሮ ይፍራ ሐሰን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ፣አቶ ሸምሰዲን መሐመድ የግብርናና የተፈጥሮ ሃብትና አቶ ካሳሁን ኃይለ ጊዮርጊስ የህግ፣ የፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት ሆነዋል።

እንዲሁም ዶክተር ዓለም ኪዳኔ የቤቶችና ማዘጋጃ ቤትና አቶ መሐመድ ዑስማን የማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሆነውም በሙሉ ድምፅ ተመርጠዋል።

ተመራጮቹ ሥራቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቃል ገብተዋል።