በግንባታ ዘርፍ የጥራት መጓደልና መጓተት ችግሮች ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

83
ደብረ ብርሀን ጥቅምት27/2011 በግንባታው ዘርፍ የሚስተዋለው የጥራት መጓደል፣ ተጀምሮ መቋረጥና የመጓተት ችሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡ በዘርፉ ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡ በሰሜን ሸዋ  ዞን የስራ ተቋራጮ  አቶ ደበበ ክንፈ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት የግንባታዎችን ጥራት ለማስጠበቅና መጓተትን ለማስቀረት  መንግስት በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ ከጨረታ አወጣጥ፣ ከዲዛይንና ከበጀት መዘግየት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ተቋራጮችና መንግስት በቅርበት አለመስራታቸው በግንባታው ጥራት ላይ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ደበበ እንዳመለከቱት ተቋራጩ የሚያገኘውን ትርፍ ብቻ በማሰብ ወቅቱን ባላገናዘበ ዋጋ ወደ ስራ በመግባት የጥራትና የስራው መጓተት ችግር እያጋጠመ ነው፤ይህንን ክህተት በመጠቀም ተቆጣጣሪዎችም ሆነ አማካሪዎች  ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ባለፈው ዓመት የመንግስትና የህዝብ ሀብት የፈሰሰበት የደብረብርሃን ከተማ ተለዋጭ አስፓልትና የደብረሲና ከተማ ደልድይ ጥቅም ሳይሰጡ መፍረሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን ሥራ ተቋራጭ አቶ ተፈራ መላኩ በበኩላቸው ለአካባቢው አፈር በቂ ጥናት አለማድረግ፣ የግንባታ እቃዎች ዋጋ መዋዠቅ፣ የግንባታ ስራን አቅም ላለው ተቋራጭ አለመስጠት፣ ተቋራጮችና የመንግስት  ባለሙያዎች በጥቅም መተሳሰር ችግሩን እንዳባበሰው ተናግረዋል። መንግስት የችግሮቹን ውስብስብነት   አጢኖ እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል ቅንጅታዊ አሰራር ማመቻቸት እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ የአማራ ክልል መንገድ፣ ህንጻ ዲዛይንና ግንባታ ባለሙያ አቶ ይመር ሙሄ  "ለችግሮች ሁሉ መንስኤ መገፋፋትና ባለሰሩት ልክ ጥቅም ለማግኘት መሞከር ነው" ብለዋል፡፡ ችግሮች ሲፈጠሩ ባለቤት ለመስጠትና ተጠያቂ ለማደረግ ሲሞከረ ችግሩ በማወሳሰብ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝዳንት ኢንጅነር አምሃ ስሜ በበበኩላቸው በጥናት የታገዝ ጥራት ያለው ግንባታ ለማካሄድ ተቋራጮች ከምንም በላይ ሙያዊ  ስነ-ምግባር ተላብሰው ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የሚወጡ ጨረታዎች ለስርቆት ምቹ በመሆናቸው ለጭቅጭቅና ጥራት የጎደለው ግንባታ እንዲፈጸም በር መክፈቱን አመልክተዋል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክትር ዶክተር ኢንጅነር አራጋው አሻ ናቸው፡፡ ለዚህም ጥናት ማድረጋቸውንና በቅርቡ መንግስት በአዲስ መልክ  እንደሚያቋቁመው የሚጠበቀው የኮንስትራክሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ችግሩን ለመፍታት እንደሚያስችልም   ጠቁመዋል፡፡ በዘርፉ በሚስተዋሉ ችሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ በተካሄደው ውይይት  ከግንባታ ዘርፍ የተወጣጡ ባለሙያዎች ፣ ተቋራጮች፣ የደብረብርሃን ዩንቨርሲቲና ሌሎችም  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም