የዘንደሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መነሻና መድረሻ ቦታ ለውጥ ተደረገ

607

አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 በመጪው ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደው የዘንደሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መነሻና መድረሻ ቦታ ለውጥ  መደረጉ ተገለፀ።

ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ የሚዘጋጀው ዓመታዊው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ወትሮ የሚካሄድበት ቋሚ መነሻና መድረሻ ቦታ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ነበር።

ሆኖም ዘንድሮ ውድድሩ ይካሄዳል ተብሎ በተያዘበት እለት ከአፍሪካ ህብረት ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ጋር በመገጣጠሙ ቦታው እንዲቀየር መደረጉን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ከሩጫው ቀን ይልቅ ሩጫው የሚካሄድበትን ቦታ መቀየር ቀላልና የተሻለው አማራጭ ሆኖ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ከመላው ዓለም የሚመጡትን ጨምሮ በጠቅላላው 44 ሺህ ህዝብ ይሳተፍበታል ተብሎ የሚጠበቀው የዘንድሮው ሩጫ መነሻና መድረሻ ቦታ ስድስት ኪሎ የሚገኘው የሰማእታት ሀውልት እንዲሆን ተወስኗል።

በዚህም መሰረት ሩጫው ከአደባባዩ በመነሳት በሚኒሊክ ሆስፒታል፣ እንግሊዝ ኤምባሲ በኩል ሾላ ገበያን በመዞር በአድዋ ደልድይ አደርጎ አራት ኪሎ ፓርላማን በማቋረጥ ስደስት ኪሎ ሰማእታት ሀውል ሲደረስ ያበቃል።

“ቀጣይ መሪ የሚሆኑ ሴት ልጆችን አሁን እናብቃ” በሚል መሪ ቃል ነው የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚካሄደው።