ምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ሳያጸድቅ ቀረ

60
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተመለከተ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ሳያጸድቅ ቀረ። 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ነው  ውሳኔውን ያሳለፈው። ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በአዲስ መልክ የተደራጀውና በቋሚ ኮሚቴ አመራሮች ላይ የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ከአባላቱ በአብላጫው ድጋፍ ባለማግኘቱ ሳይጸድቅ ቀርቷል። በዚሁ መሰረት የህግ፣ የፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር- አቶ አማኑኤል አብርሃም የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር -ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር-ወይዘሮ ፎዝያ አሚን የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር -አቶ መሐመድ የሱፍ የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር -ወይዘሮ እምዬ ቢተው የበጀት፣ገቢዮችና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር -አቶ አጽበሃ አረጋዊ የግብርናና አርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር -አቶ ጫኔ ሽመካ የተፈጥሮ ሀብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ-ወይዘሮ ፈትያ የሱፍ የከተማ ልማት፣ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር አቶ ካሚል አህመድ የውጭ ጉዳዮችና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን ደግሞ አቶ ሞቱማ መቃሳ በሊቀመንበርነት እንዲመሩ በውሳኔ ሀሳብ ተካተው ነበር። የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት የአመራር ምደባው የትምህርት ዝግጅትን፣ ልምድንና የአመራር ብቃትን ታሳቢ ያደረገ መሆን ነበረበት የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል። በተለይ ሊቃነ-መናብርቱ የሚመሩት ቋሚ ኮሚቴና የትምህርት ዝግጅታቸው አብሮ መሄድ ነበረበት ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት። ከዚህ በፊት በቸልተኝነት አጀንዳዎች ሲወሰኑ ዝም ብለው ሲመለከቱ የነበሩ አባላት በምደባው ተካተዋል፤ ይሄ አግባብ አይደለም ያሉ ሲሆን በዚህም "ፓርለማው ጥርስ የለውም" ሲባል ነበር፤ ከዚህ በኋላ የቀረበልንን ሁሉ ማጽደቅ የለብንም፤ መጽደቅ የሌለበት ነገር መጽደቅ የለበትም የሚል ሀሳብ በማምጣት የሞገቱም  ነበሩ። በአንጻሩ ሌሎች የምክር ቤት አባላት ደግሞ በአገሪቷ ውስጥ ለውጥ እየተካሄደ ባለበት ወቅት "ልክ እንደ ደሴት ለውጥ አያስፈለገንም የሚል አቋም መያዝ ተገቢ አይደለም" ሲሉም ተደምጠዋል። የውሳኔ ሀሳቡን በማጽደቅ የአፈጻጸም ችግሮች ካሉ ወደፊት እያዩ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ይሻሻል ያሉ የምክር ቤት አባላት ደግሞ "ጊዜው ከመሄዱ አኳያ ቶሎ ጸድቆ ወደ ሥራ መግባት አለበት" በሚል ተከራክረዋል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የአመራር ምደባው በተቻለ መጠን የትምህርት ዝግጅትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ጥረት መደረጉን አብራርተዋል። ''የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀትም ሆነ የአመራር ምደባው ቋሚ አይደለም አፈጻጸም እየተገመገመ ሊቀየር የሚችልበት ዕድል ይኖራል'' ሲሉም ነው ያብራሩት። የምክር ቤቱ አባላት በውሳኔ ሀሳቡ ላይ በሰፊው ከተከራከሩ በኋላ የአመራርና የአባላት ምደባው የውሳኔ ሀሳብ በይደር እንዲተላለፍ ወስኗል። በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን የሥራ ስንብት በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ሳያጸድቅ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ወስኗል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም