በሰሜን ሸዋ ዞን ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ ተጠቅመው የተገኙ ስድስት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

113
ደብረ ብርሃን ጥቅምት 26/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተጭበረበረ መንገድ የተገኘን ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ ተጠቅመው የተገኙ ስድስት ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ። በአማራ ክልል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በበኩሉ 30 ግለሰቦች በሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ ተጠርጥረው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ገልጿል። የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወይዘሪት ዘርትሁን ያዘው ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የተቀጡት ሃሰተኛ ሰነድን እውነተኛ አስመስለው ተጠቅመው መገኘታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ ነው። ከተቀጡት ውስጥም አቶ ወርቁ ኃይለየሱስና አቶ ዘነበ ተመሰለ የተባሉ ግለሰቦች በአንጎለላና ጠራ እንዲሁም በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመደበኛ የተማሩ በማስመሰል በተጭበረበረ መንገድ የ8ኛ ክፍል ሰርተፍኬትና መንጃ ፍቃድ ይዘው መገኘታቸው በማስረጃ ተረጋግጧል። ከአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 የሀሰት መሸኛ ይዘው በደብረብርሃን ከተማ የቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት የሞከሩ 4 ግለሰቦችም ከተማ አስተዳደሩ ግቢ ውስጥ እጅ ከፈንጅ በቁጥጥር ስር ውለዋል። የኋላሸት ሽፈራው፣ ለማ ይፍሩና በለጠው አንዳርጌ በሞጃና ወደራ ወረዳ ቡርቃና ፈለገ ገነት ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ መስታዋት ዳመኑ ደግሞ በደብረብርሃን ከተማ ቀበሌ 06 ነዋሪ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ወይዘሪት ዘርትሁን ገልጸዋል፡፡ የተቀጡት ሁሉም ግለሰቦች ከትምህርት ቤቶችም ሆነ ከክፍለ ከተማው በህጋዊ መንገድ ማስረጃውን ያመጡ ስለመሆናቸው ተቋማቱ ድረስ በመሄድ ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቁመው፣ በእዚህም ሰነዶቹ የተጭበረበሩና ህጋዊ ያልሆኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። ግለሰቦቹ በተከሰሱባቸው የማጭበርበር ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸው በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰሞኑን በዋለው ችሎት ከአንድ ዓመት ከ6 ወር እስከ አንድ ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራትና ከአንድ ሺህ እስከ 3 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት  እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል። በአማራ ክልል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን የደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ አበበ በበኩላቸው በሰነድ ማጭበርበር ወንጀል የተከሰሱ 30 ግለሰቦች በሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃ ተጠርጥረው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል። በአማራ ክልል ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃን ለማምከን በተደራጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም