ትምህርት ቤቶቹ የትምህርት መርጃ ግብዓት ማሟላት ላይ ሊሰሩ ይገባል-የአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ

57
አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2011 በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት መርጃ ግብዓት ማሟላት ላይ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ። የአዲስ አበባ አጠቃላይ ትምህርት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ በመዲናዋ ትምህርት ቤቶች አጠቃላይ ሁኔታ ላይ ውይይት አድርጓል። ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የሚጠበቅባቸውን ዝቅተኛ ውጤት በመሟላት ነው እውቅናና የፍቃድ እድሳት የተደረገላቸው። በ363 ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጥናቱ በቅድመ መደበኛ፣ በአንደኛ፣ በሁለተኛና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ላይ የተለያዩ የትምህርት ግብዓት ማሟላት ላይ ችግሮች ይስተዋልባቸዋል። ከሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ጋር ተያይዞ ለፊዚክስ፣ ለባዮሎጂና ለኬሚስትሪ የትምህርት ዓይነቶች በቂ ቤተ-ሙከራና ቁሶች  አለመኖራቸው  ተገልጿል። እንደ ሪፖርቱ ገለጻ፤ ቤተ-ሙከራዎቹ የማሳያ ክፍል፣ የመምህራን ማዘጋጃና የመሣሪያ ማስቀመጫ የተባሉ ሦስት ክፍሎች እንዲኖሩት ቢጠበቅም አብዛኛዎቹ አንድ ክፍል ነው ያላቸው። በተመሳሳይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም አብዛኞቹ ቤተ-ሙከራዎች ቢኖሯቸውም በቂ መሣሪያና ግብዓት እንደሌላቸው ተጠቅሷል። በቅድመ-መደበኛም ለህጻናቱ ከሚያስፈልጉ በቂ የቅጥር ግቢና የማሸለቢያ ክፍል አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም በመማር ማስተማሩ ላይ አዋኪ መሆኑን ጠቅሰዋል። በኤጀንሲው የአጠቃላይ ትምህርት ተቋማት ዳይሬክተር አቶ ዘመኑ አብዩ፤ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችን ለመፍታት ኤጀንሲው በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል። ባለፈው ዓመት ችግሩ የተለየባቸው ትምህርት ቤቶች ግብረ መልስ መቀበላቸውን ጠቅሰው በምን መልኩ እየተገበሩት መሆኑን ክትትል እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል። የቁጥጥር ሥርዓቱ በመደበኛነት የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው፤ ኤጀንሲው የሚሰጣቸውን ግብረ መልሶች በአግባቡ ተግባራዊ በማያደርጉ ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም