በአክሱም ከተማ ሦስት የግል ኮሌጆች ተዘጉ

68
አክሱም ጥቅምት 25/2011 በትግራይ ክልል በአክሱም ከተማ ከተሰጣቸው ፈቃድ ውጭ ፈጽመው የተገኙ  ሦስት የግል ኮሌጆች  ተዘጉ፡፡ የከተማው ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክለማርያም ካሕሳይ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮሌጆቹ የተዘጉት መሠረታዊ የአሰራር ጥሰት ፈጽመው በመገኘታቸው ነው። ውሳኔው የተላለፈባቸውከክልሉ ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ እውቅና ተሰጥቷቸው በመማር ማስተማር ሂደት ላይ የነበሩት ዊነር፣ሸባና ኒው ላይፍ  የተባሉ ኮሌጆች ናቸው፡፡ ኮሌጆቹ  ችግሮቻቸውን  በወቅቱ  እንዲያርሙ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፤ለውጥ ሊያመጡ አለመቻላቸውን አቶ ተክለማሪያም ተናግረዋል፡፡ ኮሌጆቹ  ከተሰጣቸው እውቅና ውጭ ስልጠና በመሰጠት፣ፈቃዳቸውን ባለማደስና ለሰልጣኞች በጊዜው የምዘናና የብቃት ማረጋገጫ ፈተና አለመስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም የሰልጣኞችን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆንና የሚሰጡት ትምህርትና ስልጠና የጥራት ችግር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ በተለይም ዊነር ኮሌጅ ከተሰጠው ደረጃ እውቅና ውጭ በደረጃ ሶስትና አራት በድብቅ ሲያሰለጥን በመገኘቱ ኮሌጁ ለፈጸመው ጥፋትና ተማሪዎቹ የከፈሉት ገንዘብ እንዲመልስ በህግ እንዲታይ መወሰኑንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በኮሌጆቹ  በተለያዩ ደረጃ ሲሰለጥኑየነበሩ ተማሪዎችም ወደ መንግስት ኮሌጅ እንዲዛወሩ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ የዊነር ኮሌጅ የሁለተኛ አመት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  ተማሪ የነበረችው አልማዝ ፍስሃ መንግስት ተማሪዎቹን በመንግስት ኮሌጅ ገብተው ትምህርታቸው እንዲከታተሉ የወሰደው ውሳኔ እሷን ጨምሮ ሌሎች የኮሎጁ ተማሪዎች እንዳስደሰታቸው ገልጻለች፡፡ የኒው ላይፍ ኮሌጅ ባለቤት አቶ መሓሪ  ወልደማሪያም በበኩላቸው ፈቃድ ባለማሳደሳቸው ኮሌጁ መዘጋቱን ተናግረዋል፡፡ ፈቃድ ለማሳደስ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ጽፈው ምላሽ እንዳላገኙና ኮሌጁ በዚህ ምክንያት እንዲዘጋ መደረጉ አግባብነት  የለውም ብለዋል። የሸባና ዊነር ኮሌጅ ባለቤቶችና የስራ ሀላፊዎች የኢዜአ ሪፖርተር በአካልና በስልክ ለማግኘት ያደረገው  ጥረት አልተሳካለትም፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም