መከባበርና መመሰጋገን በአገር ደረጃ ባህል ሆኖ ሊቀጥል ይገባል-ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ

69
አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 መከባበርና መመሰጋገን በአገር ደረጃ ባህል ሆኖ መቀጠል እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ትናንት ማምሻውን በብሄራዊ ቤተ መንግስት ለቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ለቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዳኜ መላኩ የተከናወነው የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ላይ ነው። በፕሮግራሙ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለአገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ኒሻንና ዲፕሎማ የተበረከተላቸው ሲሆን ለባለቤታቸው ወይዘሮ መዓዛ አብርሃምና ለቀድሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዳኜም ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ሽኝት የተደረገላቸው የቀድሞ ባለስልጣናት በዚህ መርሃ ግብር ላይ እንዳሉት ለአገር አገልግሎት ሲባል ለተተኪ  ቦታን መልቀቅ ትልቅ ክብር እንዲሰማቸው እንዳደረገና የዴሞክራሲ ባህልን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዶክተር አብይ የተጀመረው ይህ ተግባር ሊበረታታ የሚገባ ነው በማለት የገለጹ ሲሆን ያላቸውን ምስጋናም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። ''ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ለኔ ያደረጉት አሸኛኘትና አዲስ ለተሾሙት ፕሬዝዳንት ያደረጉት የአቀባበል ፕሮግራም  ለሐገራችን ያሳዩትና የተከሉት አዲስ የዴሞክራሲ ባህል ስለሆነ፣ ይህን ታሪካዊና ዘመን ተሻጋሪ ስራቸውን እንደማደንቅ እየገለጽኩ እዚህም የተገኛችሁ እንድታመሰግኑ እጠይቃለሁ።''ያሉት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ከመንግስት ስልጣን ቢያርፉ በቀጣይም በየትኛም ጊዜ የአገር ጥሪን ተቀብሎ ለመስራት ዝግጁ ነኝም ብለዋል ዶክተር ሙላቱ። ''እኔም የዚህ ታሪክ ሰሪ ትውልድ አባል በመሆኔ የተሰማኝን ደስታ እየገለጽኩ አገርና ህዝብ ከኔ የሚፈልጉትን መወጣት ይገባል ብዬ አምናሁ።  ቀጣይ ጊዜዬንም ከግል ጥቅምና ፍላጎት በላይ የአገር ጥቅምና ፍላጎት ማስቀደም እመርጣለሁ።  የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ አገራዊ አንድነት ለማጠናከርና ዜጎቻችን ሁሉ የሚያሳትፍ እንዲሆን ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኔን ቃል እገባለሁ። የቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዳኜ መላኩ በበኩላቸው ''የጤና ሁኔታ እየገፋ መጥቶ፣ ከስራዬ በፍቃደኝነት ልሰናበት ተገደድኩ እንጂ፣ ከአዲሱ አመራር ጎን ሆኜ ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኔን አረጋግጣለሁ፣ ለአገርና ለህዝብ  ስታገለግል ቆይተህ በክብር መሸኘትን የሚያክል ክብር የለም።''ብለዋል፡፡ በመድረኩ ንግግር ያደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ለህዝብ ጥሩ ነገር ሰርቶ፣ ለአገር በታማኝነት አገልግሎ መውረድ ክብር መሆኑ ባህላችን መሆን ይገባዋል ብለዋል። በታማኝነት ላገለገሉና ለአገር ባለውለታ ለሆኑ ሰዎች ክብርና ምስጋና መስጠትም እንደ ልማድ ልንይዘው ይገባል ብለዋል። ''በጋራ ገበታ የምንቀርብበት ማዕድ የምንቆርስበት ባህል ባለመኖሩ፣ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር እያሉ መጥራት እምብዛም ያልተለመደ ተግባር ነው። ይሁን እንጂ ከባህላችን ፣ከሃይማኖታችን፣ ከማንነታችን አንጻር ሲታይ እንደ ኢትዮጵያዊ ያገለገለን የሚያከብር ታሪክ የሚወድና የሚመጻደቅበት ባለመኖሩ፣ ከእንግዲህ በኋላ ይህ ልማድ ሰልጥኖ ባህላችን እንዲሆን ማገልገል የሚያስከብር ስንወጣም ደግሞ በምስጋና እንዲሆን እንደ ልማድ እንዲጎለብት ስለምንፈልግ  ተሿሚዎች ተመርጦ ማገልገል ተመስግኖ መሰናበት፣ ከዚያም በኋላ በምክር ማገልገል እስካሁን ያልነበረ ባህላችን ለማስጀመር ለማጎልበት ካለን ፍላጎት ሁሉም ጉዳዩ በተገኘበት ማክበር ለትውልድ ከምናወርሰው ቅርስ አንዱ አንዲሆን ስለምንፈልግ ጭምር ነው።'' እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሁሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅም የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ላበረከቱት አስተወጽዖ ምስጋናቸውን ቸረዋል። ክቡር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሀገራቸውን በከፍተኛ ታማኝነት ታታሪነት፣ ትጋት ያገለገሉ ሰው ናቸው በፕሬዝዳንትነት ከዚያ በፊት ያለውን ህይወታቸውን እኔ አውቃለው፣ አንድ ላይ የቅርብ የስራ ባልደረባዬ ሆነው ሰርተዋል።ለዚህም በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ሆኜ በራሴም ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ።" በመድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅን ጭምሮ ሶስት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም