ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 15 ዘመናዊ የዊልቸር አበረከቱ

84
አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታየቸው ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የዊልቸር ድጋፍ አደረጉ። ቀዳማዊ እመቤቷ የ2011 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን የምሳ ግብዣ ባደረጉበት ወቅት ባለቤታቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማዕከሉን እንደሚጎበኙ ቃል መግባታቸው ይታወሳል። በመሆኑም ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ማዕከሉን ከጎበኙ በኋላ የ15 ዘመናዊ ባለሞተር ዊልቸር ድጋፍ አድርገዋል። ድጋፉ የሚውለውም በማዕከሉ በከፋ የእንቅስቃሴ እክል ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መሆኑ ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን  በራሳቸው ወገን ሲደገፉ ማየት ጥልቅ  ሞራልና  ተስፋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። እውነተኛው አክሊል የሚገኘውም እንደዚህ አይነቱን ተግባር በመፈጸም ነው ሲሉም አሳስበዋል። ''መናገር የማይችሉ እራሳቸውን መቆጣጠር የማይችሉ ሰዎችን የሚያየን ያየናል ብለው በንጹህ ልቦና ማገልገል መታደል ነው። እውነተኛው አክሊል የሚገኘው ከእንደዚህ አይነት ስፍራ ነው።እውነተኛውን የሚሹ ሰዎች ዝቅ ብለው መደገፍ የሚገባቸውን ሲደግፉ ሲያግዙ ማየት በኢትዮጵያ እንደዚህም አይነት ስራ የሚሰሩ ግለሰቦችን ማየት ጥልቅ ሞራል ተስፋ የሚሰጥ ነው።” የኢትዮጵያ ህዝብ ደግና ሩህሩህ በመሆኑ ማዕከሉን  በቀጣይነት እንደሚደግፍ እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ እርሳቸውም በተቻላቸው አቅም በማዕከሉ ያሉ አረጋውያንንና የአእምሮ ህሙማንን ለመጎብኘት ቃል ገብተዋል። ''እኔ ልነግራችሁ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ህዝብ ደግ ህዝብ ነው። የማየት እድል ካገኘ ይህን የተቀደሰ ዓላማና ተግባር በመደገፍ ከጎናችሁ ሆኖ አልባሌ ቦታ የሚባክን ጉልበትና ሃብት ሰብስቦ እናንተን በማገዝ ከጎናችሁ በመሆን ቤተሰብ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ሙሉ እምነት አለኝ ፤እኔም አቅሜ በፈቀደ መጠን እናንተን በመጎብኘት ከጎናችሁ እንደምሆን ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።” የማዕከሉ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በተለይም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚንስትሩን አርአያ በመከተል በማዕከሉ የሚገኙ ወገኖቻቸውን እንድጎበኙ ጥሪ አቅርቧል። ለመልካም ስራ ጊዜ መስጠት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም። '' የዶክተር አብይን አርአያ ተከትለን ዛሬ መጥተው በመጎብኘታቸው ማንም ሰው ከፈለገ ጊዜ እንዳለውና ለእግዚአብሄር ስራ ጊዜ ሊያንሰው እንደማይገባ ስለአስተማሩን፤ ከእርሳቸው የበለጠ ጊዜ የሌለው ሰው የለም፤ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር እየመሩ ጊዜ የለኝም ቢሉ ተቀባይነት አለው።እና ሁላችሁም የመንግስት ሰራተኞችም ብትሆኑ፣ ሚንስትሮችም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል ሰዎችን በመርዳት ከእግዚአብሄር ዋጋ እንድናገኝና በዚህ ውሸት በሞላበት ዓለም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመግለጽ እወዳለሁ።” ቀዳማዊ እመቤቷ ያደረጉት ድጋፍም ለማዕከሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግሯል። የመቄዶንያ የአረጋውያንና አእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አርባ አረጋውያንና አእምሮ ህሙማን በመያዝ የተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን፤  ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ወገኖች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም