በትግራይ በሄክታር ከ580 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጠው የቲማቲም ዝርያ በሌሎች አካባቢዎች ይስፋፋል

1528

መቀሌ ጥቅምት 23/2011 የትግራይ ክልል በክልተ አውላሎ ወረዳ በሄክታር ከ580 ኩንታል በላይ ምርት የሰጠውን የቲማቲም ዝርያ በሌሎች አካባቢዎችም እንደሚያስፋፋ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባለፈው ዓመት በ16 የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች የተካሄደው ሙከራ ውጤት አስገኝቷል።

በቢሮው የሆርቲካልቸርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ በሪሁ አረጋዊ ለኢዜአ እንደገለጹት በወረዳው በሙከራ ከፍተኛ ምርት ያስገኘውን “ገሊላ’’ የተባለ የተዳቀለ ዝርያ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው።

በአጉላዕ ቀበሌ መስኖ ተጠቃሚ በሆኑ 16 አርሶ አደሮች በተካሄደው ሙከራ የተገኘው ውጤት በምርታማነቱና በውፍረቱ የተሻለ ነው።

ሥራው በበጋው ወቅት በሁሉም ቲማቲም አብቃይና የመስኖ ተጠቃሚ ሞዴል ወረዳዎች  እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እስካሁን እየተጠቀመበት ያለው የቲማቲም ዝርያ በሄክታር ከ160 ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደማይሰጥ ነው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣

ምርቱ አነስተኛ፣ፍሬና ውሃ የበዛበት በመሆኑ ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ አመቺ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

በአንጻሩ “ገሊላ’’ የተባለው የቲማቲም  ዝሪያ ፍሬው አነስተኛ፣ሙሉ ሰውነቱ በቲማቲም ስጋ የተሞላ በመሆኑ ’’ሳልሳ’’ ለመስራት ምቹ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ በበጋ ወቅት 68 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የልኬት ስራ በጂ ፒ ኤስ (በዘመናዊ የመለኪያ መሳሪያ) መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በመስኖ የሚሳተፉ ከ200 ሺህ አርሶ አደሮች ስልጠና ለመስጠት ዝግጅቱ መጠናቀቁን አቶ በሪሁ ተናግረዋል፡፡

በክልተ አውለዓሎ ወረዳ ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የመስኖ ባለሙያ አቶ ካህሳይ ባሪያብሩክ ባለፈው ዓመት በወረዳው በውስን አርሶ አደሮችና በአነስተኛ መሬት የተካሄደው ሙከራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሙከራው የተካሄደባቸው አርሶ አደሮች ለውጤት የበቁት መሬታቸውን አለስልሰውና በማዳበሪያ ተጠቅመው መሆኑንም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

በዚሁ ወረዳ የአጉላዕ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ገሊላ የተባለው ቲማቲም በእርሻ መሬታቸው ሙከራ ከተካሄደባቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አብርሃ ኪሮስ አንዱ ናቸው፡፡

ከሄክታር ከ580 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ፣ ያለሙት አዲስ የተዳቀለ የቲማቲም ምርጥ ዘር ወደ ውጤት የተቀየረው በባለሙያዎች ልዩ ድጋፍና ክትትል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር በርሀ አባይ በበኩላቸው ካለሙት ሄክታር ቲማቲም 500 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ምርታቸውም በገበያ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በወረዳው ባለፈው ዓመት 192 ሺህ አርሶ አደሮች ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ መስኖ አልምተው ከ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡