ስዊዲን ለኢትዮጵያ የልማት እቅድ የምትሰጠውን ድጋፍ ትቀጥላለች - በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር

68
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 የስዊዲን መንግስት በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ የልማት መርሃ-ግብሮች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። በኢትዮጵያ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነም በኢትዮጵያ የስዊዲን አምባሳደር ገልፀዋል። አምባሳደር ቶርብዮን ፒተርሰን ከኢዜአ ጋር ባካሄዱት ቃለ-ምልልስ  በተለይም በአገራቱ መካከል ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተቀየሰው የልማት ትብብር መሰረት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው። የፆታ እኩልነትና ሰብአዊ መብትን ማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን ማጠናከር፣ ዲሞክራሲን ማጎልበትና የሚዲያ ነጻነትን ማሳደግ ከትብብር መርሃ-ግብሮቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እንዲሁም የግል ዘርፉን ልማት ለማጠናከር በሚያስችሉ ዘርፎች ላይም ሁለቱ አገራት በትብብር እየሰሩ ነው ብለዋል። ከከፍተኛ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ጋር በተደረገ ትብብር መሰረትም ቤተ-ሙከራን ጨምሮ ተቋማቱን በተለያዩ መሳሪያዎች የማጠናከርና ምሁራንን የማሰልጠን ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት። የስዊዲን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የልማትና ቴክኒክ ድጋፍ ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። አምባሳደሩ አክለውም የስዊድን ኩባንያዎች መዋእለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ በማፍሰስ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እና የስራ ፈጠራ ሥራን ለማስፋፋት ጥረት ይደረጋል ብለዋል። በኢትዮጵያ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነም ነው አምባሳደሩ ያመለከቱት። ኢትዮጵያ በቅርቡ ሴት ርእሰ ብሄር መምረጧን ጨምሮ በካቢኔ ውስጥ  የሴቶች ተሳትፎ ወደ50 በመቶ እንዲያድግ መደረጉ አገሪቱ የፆታ እኩልነት እውን ይሆን ዘንድ እያከናወነች ያለው ጥረት ማሳያ መሆኑን በመጠቆም። ስዊድን የልማት አጋሮቿ የሴቶችን ተሳትፎና ወደአመራርነት ለማምጣት የሚያከናውኑትን ጥረት ትደግፋለች። በተለይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአፍሪካውያን ብሎም ለኢትዮጵያውያን ወደር የሌላቸው አርአያ መሆናቸውን ገልፀው በአገሪቱ ሴቶችን ወደአመራርነት በማምጣት እኩልነትን ለማረጋገጥ የተሰራውን ተግባር አድንቀዋል። ከንጉሳዊስ ስርዓት ጀምሮ የተመሰረተው የኢትዮጵያና ስዊዲን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዘርፉን እያሰፋ በአሁኑ ወቅት የሚያበረታታ የምጣኔ ኃብትና ልማት ትብብርን መቀዳጀት እንደቻለ ይነገራል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ስዊዲን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው በመሥራት ላይ መሆናቸው ነው። "ኤች እና ኤም" የተሰኘውን ግዙፍ የጨርቃጭርቅና አልባሳት ኩባንያን ጨምሮ ኤሪክሰን፣ ቮልቮና ስካኒያ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የአገሪቱ ኩባንያዎች መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም