ሠላማዊ የመማር ማስተማር ስራን የሚያውኩ ተግባራትን ለመከላከል የህብረተሰቡ ድጋፍ ተጠየቀ

45
ሶዶ ጥቅምት 22/2011 ሠላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን በማወክ የተማሪውን ውጤት የሚያበላሹ ተግባራትን ለመከላከል ህብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ህገ  ወጥ ተግባራትን መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ ከሶዶ ከተማ ማህበረሰብ ጋር ተወያይቷል፡፡ በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲዉ አካዳሚክ ምክትል ፕረዝዳንት ዶክተር ወንድሙ ወልዴ እንደተናገሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት የአካባቢውን ህብረተሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል፡፡ ሆኖም በትምህርት ተቋማት አከባቢ ኃላፊነት የጎደላቸው የንግድ ድርጅቶች ለአደገኛ ዕጾች መሸሸጊያ ከመሆን ባሻገር ተማሪዎችን ላልተፈለጉ ተግባራት እየዳረጉ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ለጸጥታ ችግሮች ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ገልጸው ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን በማወክ የተማሪውን ውጤት የሚያበላሹ ተግባራትን ለመከላከል የህብረተሰቡን የተቀናጀ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡ ጫት፣ ሺሻና መጠጥ ቤቶችን ጨምሮ ወጣቱን ለጥፋት ብሎም ለጤናና ስነ ተዋልዶ በሽታዎች እንዲጋለጡ የሚያደርግ መሆኑን ዶክተር ወንድሙ ተናግረዋል፡፡ በኩረጃ የሚያምን ትውልድ እንዲፈጠር እያደረገም በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው የንግድ ተቋማት አደረጃጀት የሚፈቅደውን የህግ አሰራር በመከተል ከአከባቢው የማስነሳት ተግባር ያከናውናል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዉ የኤች አይ ቪ ኤድስና ስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክተር አቶ እሼቱ አየለ በበኩላቸው የነጋዴዎችን ግንዛቤ በማሳደግ በሌላ እንዲሰማሩ፣ በሱስ የተጠቁ ተማሪዎችን የማማከርና የማገገም ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉት የሃገር ሽማግሌ አቶ ዛና ጃፎ ተቋሙ  ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩ ህገ ወጥ ተግባራትን በኃላፊነት ለመከላከል እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ የራሱን ልጅ እያሰበ መስራት እንዲችል በመቀስቀስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸው "ዩኒቨርሲቲዉ የራሱን ህግና ደንብ ከማስከበር አንጻር የሚታይበትን ክፍተት ሊሞላ ይገባል" ብለዋል፡፡ ከፋና ቀበሌ የመጡት ወይዘሮ  ትሩንጎ ኮራ ሊማሩ የመጡ ወጣቶች የእጽ ተጠቂ ሆነው ማየት እየተለመደ በመምጣቱ ለንግድ ተቋማት ህጋዊ መስመር አለማበጀቱ የችግሩ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ "ችግሩን ከመሰረቱ ለማስወገድ ህብረተሰቡና የጸጥታ ኃይሉ ከዩኒቨርስቲው ጎን ሊሆነ ይገባል" ብለዋል፡፡ ለተለያዩ ሱሶች የሚያጋልጡ አደንዛዠ ዕጽ ተጠቃሚዎችና አዘዋዋሪዎችን ለመከላከል ፖሊስ እንደሚሰራና ለዚህም የህዝቡ ትብብር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የመርካቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዠ ረዳት ኢንስፔክተር አበባየሁ አንጁሎ ናቸው፡፡ "በአካባቢው አስተማማኝ ጸጥታን ለማስፈንና  አላስፈላጊ የንግድ ተቋማትን ህጋዊ ሂደትን ተከትለን የማስቆም ስራ ጀምረናል" ብለዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የኃይማኖት መሪዎች ፣ የሃገር ሽማግሌዎች ፣የንግድ ማህበረሰብ ፣የጸጥታ አካላትና የተማሪ ተወካዮች  ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም