አርሶ አደሮቹ የዝናብ ውሃን ለመጠጥ አገልግሎትና ለጓሮ አትክልት በማዋል ተጠቃሚ ሆነናል አሉ

118
አዳማ ጥቅምት 22/2011 የዝናብ ውሃን ለመጠጥ አገልግሎትና ለጓሮ አትክልት ልማት እያዋሉ መሆኑን በምስራቅ ሸዋ ዞን የአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። በቻይና የድህነት ቅነሳ ፋዎንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ በአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የተገነቡ 41 የዝናብ ውሃ ማጠራቀሚያ ፕሮጀክቶች ዛሬ ተመርቀዋል። ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት የወረዳው ነዋሪዎች መካከል የጎልባ አሉቶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቴሴ መገርሶ አካባቢያቸው የመጠጥ ውሃ እጥረት የሚታይበት ከመሆኑም ባሻገር፤ የከርሰ ምድር ውሃ በፍሎራይድ ኬሚካል በመጠቃቱ በመሆኑ ችግር እንደነበረበት ገልጸዋል። የመጠጥ ውሃ አገልግሎት የሚያገኙት ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ከዝዋይ ከተማ በጋማ ከብት እያመላለሱ መሆኑንም ተናግረዋል። መንግሥት በቀያችን አዲስ ቴክኖሎጂ በመገንባት በክረምት ወራት የዝናብ ውሃን በማጠራቀም ለአነስተኛ የጓሮ አትክልት ልማትና ለመጠጥ እንድንጠቀም ገንብቶልናል ብለዋል። በዚሁ ወረዳ የአናኖ ሺሾ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሃሊማ ጉዮ በበኩላቸው ወረዳው የዝናብ እጥረት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ  በመጠጥ ውሃ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በቀበሌያቸው ፕሮጀክቱ ተገንብቶ የንፁህ መጠጥ ውሃ  ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮ ሃሊማ፣ በቀጣይ በማሳቸው የጓሮ አትክልት በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ የዝናብ ውሃ አጠቃቀም ማህበር ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ምንያህል ፍቃደ  ማህበራቸው መንግሥት መድረስ  በማይችልባቸው  አካባቢዎች የኅብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ማህበራቸው ከቻይና የዝናብ ውሃ ልማትና ድህነት ቅነሳ ፋዎንዴሽን ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ 41 የዝናብ ውሃ ማጠራቀሚያ ፕሮጄክቶች ገንብቶ አገልግሎት ጀምረዋል ብለዋል። ይሄም የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ከማቃለሉም ባለፈ፤ ከ40 በላይ አባወራዎችና እማወራዎች በአነስተኛ የጓሮ አትክልት ለማልማት እንደሚያበቃቸው አመልክተዋል። የቻይና የዝናብ ውሃ ልማትና ድህነት ቅነሳ ፋዎንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ዥያን ኩዋንግ  በኢትዮጵያ  የሚስተዋለውን ድርቅና የውሃ እጥረት ለመቋቋም በዝናብ ውሃ ልማትና አጠቃቀም ላይ አገራቸው ያላትን ተሞክሮ እያስተዋወቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ድርጅታቸው ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ በመመደብ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ በሁለት ቀበሌዎች የዝናብ ውሃ ማጠራቀሚያ ፕሮጀክቶች በመገንባት ለአርሶ አደሩ ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡ ሥራውን በወረዳው በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች ለማዳረስ አርሶ አደሩን በልማት ቡድኖችና ተደራጅተው እንደሚሰሩ የወረዳው የእቅድና የምጣኔ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደበላ ፈዬ ተናግረዋል። ለአገልግሎት የበቁት የውሃ ማጠራቀሚያዎች እያንዳንዳቸው ከ15 ሺህ እስከ 20 ሺህ የሚደርስ ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው ሲሆን፣ ለመጠጥና ለአነስተኛ መስኖ ልማት አገልግሎት ይውላሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም