የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር የተማሪ ምገባ ፕሮግራም ተጀመረ

112
አዲሰ አበባ ጥቅምት 22/2011 የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር ከቻይና ሲኤፍፒኤ ፋውዴሽን ጋር በጋራ በመሆን ለ517 ተማሪዎች የሚያደርገውን የምገባ ፕሮግራም አስጀመረ። የምገባ ፕሮግራሙ የሚደረገው በልደታ ክፍለ ከተማ መተባበር 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚገኙ ተማሪዎች መሆኑ ተገልጿል። የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ልዑልሰገድ እንደገለጹት፤ የምገባ ፕሮግራሙ በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ህጻናት ተማሪዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ ሚና አለው። እንዲህ አይነቱ በጎ ተግባር "ተማሪዎች በትምህርት እንቅስቃሴያቸው ላይ መነቃቃትን ለመጨመርና አላስፈላጊ የስነ-ምግባር ችግሮችን ለማስወገድም ያስችላል" ብለዋል ። ይህም ህጻናት ተማሪዎች ወደፊት የሚያስቡበትና የሚያልሙት ደረጃ ላይ እንዲደርሱና ውጤታማ ትውልድ እዲበራከት በማድረግ ረገድም ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ሲሉም ገልጸዋል። በምገባ ማስጀመር ፕሮግራም ላይ የተገኙት የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በኩላቸው በመተባበር ትምህርት ቤት አንድም ልጅ ሳይቀር ሁሉም ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሙ ተካፋይ እንዲሆኑ ላገዙት የቻይና ኮቬርቲ አልቬሽን ፋውንዴሽን  ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይህ የምገባ ፕሮግራም እንዲጀምር የትምህርት ቤቱ አካላት፣ ወላጆችና የአካባቢው ህብረተሰብ ለዚህ ስራ ውጤታማነት እያበረከቱ ያሉትንም አስተዋጽኦ አበረታተዋል። የተመጣጠነ ምግብ ያለማግኘት ችግር ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ ከማድረጉም ባሻገር ልጆች ባሉበት እውቅት የመገብየት  አቅማቸውን በማሳጣት ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደርጋል። በመሆኑም ይህ አይነቱ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። በምገባ ፕሮግራሙ ላይ ከተገኙ ወላጆች መካከል አቶ ጸጋዬ ወንድሙና አቶ ያሲን መሐመድ  እንዳሉት ፤ የዚህ አይነቱ ፕሮግራም መኖሩ በተለይ የችግረኛና ረዳት የሌላቸውን ህጻናት ተማሪዎች ያግዛል። ይህም ተማሪዎቹን በጥሩ ሞራል እንዲማሩና ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባሻገር ለወላጆች ትልቅ ተስፋ የሚያጭር መሆኑን ገልጸው ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም