በአዲስ አበባ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖች የተቋቋሙበትን አላማ እየፈፀሙ አይደለም- ጥናት

259
አዲስ አበባ ጥቅምት 23/2011 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖች የተቋቋሙበትን አላማ እየፈፀሙ እንዳልሆነ ኢዜአ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖችን የስራ እንቅስቃሴና ችግሮችን አስመልክቶ ያደረገው የህዝብ አስተያየት ጥናት አመላክቷል። የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ በበኩሉ ማህበራቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ መፈጸም የሚያስችላቸውን ፌዴሬሽን ለመመስረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል። አዲስ የሚመሰረተው የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ፌዴሬሽን  በከተማዋ የሚገኙ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ያለባቸውን የአቅርቦት ክፍተት ይሞላል ተብሏል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ከአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር  በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖች የስራ እንቅስቃሴና በችግሮች ዙሪያ ያጠናው ጥናት እንዳመለከተው የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖች የተቋቋሙበትን አላማ በሚጠበቀው ልክ እየፈፀሙ አይደለም። ጥናቱ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት አባላትንና ዩኒየኖችን ጨምሮ 312 መሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት፣ የክፍለ ከተማና ወረዳ ህብረት ስራ ማህበራት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችንና ሰራተኞችን በማካተት የተሰራ ነው፡፡ የጥናቱን ግኝት አስመልክቶ 300 ከሚደርሱ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት የኢዜአ ህዝብ አስተያየት ጥናት ከፍተኛ ተመራማሪው አቶ ዳግም መርሻ እንዳብራሩት፤ የህብረት ስራ ማህበራቱ ለአባሎቻቸው የስልጠና፣ የማማከር፣ የመጋዘን እና የመረጃ አገልግሎት የመስጠት፣ የገበያ ትስስር ማመቻቸትና ምርቶችን የማከፋፈል ሀላፊነት ቢኖርባቸውም በተግባር እየፈፀሙት አይደለም።   የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩንየኖች መሰረታዊ ፍጆታዎችን በጥራትና በሚፈለገው መጠን አለማቅረባቸው፣ የአደረጃጀትና የካፒታል አቅም ማነስ፣ በቂና ብቃት ያለው የሰው ሀይል እጥረት፣ የገበያ ትስስር አለመጠናከር፣ የአመለካከትና የክህሎት ክፍተት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ዘመናዊ የአሰራር ስርአት አለመዘርጋት በጥናቱ የተለዩ ችግች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ዋናው መንስኤ ማህበራቱ እየገጠማቸው ያለው የገንዘብ ችግርና የአመራሮች ብቃት ማነስ መሆኑን ነው ጥናቱ ያመላከተው። ጥናቱ እንደጠቆመው ማህበራቱ የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በጥናቱ የተለዩ ችግሮች በኤጀንሲው የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሊፈቱላቸው ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው አሊ ህብረት ስራ ማህበራቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ በተሻለ መንገድ እንዲፈጽሙ ለማድረግ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ፌዴሬሽንን ለመመስረት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። በመዲናዋ የሚገኙ ህብረት ስራ ማህበራትን በማጣመር በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ፌደሬሽኑ እንደሚመሰረትም ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡ የፌደሬሽኑን የገንዘብ አቅም በማጠናከር  አቅርቦቱን በሚፈለገው ጊዜ፣ ጥራትና መጠን ለማቅረብ በሚያስችል መልኩ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት። በአዲስ አበባ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው ከ11 ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራት አሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም