አንድ መቶ ወረዳዎች የጤና መድን አገልግሎት ሽፋን ሊያገኙ ነው

2139

መቀሌ ጥቅምት 22/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ በተያዘው በጀት ዓመት ተጨማሪ 100 ወረዳዎች የጤና መድን አገልግሎት ሽፋን እንደሚያገኙ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል በጤና መድን አገልግሎቱ ሞዴል በመሆኑ ወረዳዎች ሰሞኑን የመስክ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግባራ ዘመን በሃገሪቱ በ522 ወረዳዎች የጤና መድን አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

በዚህም በተለይ በትግራይ ፣አማራ ፣ኦሮሚያና ደቡብ ክልል ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎቱን ለማስፋት በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤት መገኘቱን ገልዋል።

በተሰበሰበው የአባልነት ክፍያ ከ17 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በየአካባቢያቸው በሚገኙ ጤና ተቋማት  የሚፈልጉትን የህክምና አገልግሎትና መድኃኒት እንዲያገኙ መደረጉን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

” በዘርፉ ከዚህ በላይ መስራት ይቻል ነበር ” ያሉት ዶክተር አሚር፣ በሃገሪቱ አንዳንንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከትና ያለመረጋጋት በስራው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

የቀሩ ስራዎችን ለማካካስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአጋሮቹ ጋር  በመቀናጀት በተያዘው የበጀት ዓመት ተጨማሪ 100 ወረዳዎች የጤና መድን አገልግሎት ሽፋን እንደያገኙ ለማስቻል ታቅዶ  እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

” የታቀደውን የጤና መድን አገልግሎት ለማሳካት ለጤና ባለሙያዎች ብቻ የሚተው አይደለም፤ በየደረጃው የሚገኝ የህዝብና የመንግስት መዋቅሮች ስራችን ነው ብለው በትጋት መስራት ይጠበቅባቸዋል “ብለዋል።

በትግራይ ክልል በጤና መድን አገልግሎት ሞዴል ከሆኑ አባላት መካከል በክልተ አውላዕሎ ወረዳ የገማድ ቀበሌ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ንግስቲ አንዷ ናቸው፡፡

የጤና መድን አገልግሎት አባል ከመሆናቸው በፊት ልጆቻቸው ሲታመሙ ለማሳከም እስከ ሦስት ሺህ ብር ድረስ ወጪ ይጠይቃቸው እንደነበር በሰጡት አስተያየት አውስተዋል።

አባል ከሆኑ ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በዓመት 240 ብር ብቻ የአባልነት ክፍያ በመፈጸም ያለ ምንም ችግርና ውጣ ውረድ የሚፈልጉትን የጤና አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው ለሚገኙ 30 የሚሆኑ ሴቶችም የጤና መድን አባላት እንዲሆኑ በማነሳሳት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ገብረህይወት አብርሃ በበኩላቸው ” የጤና መድን አገልግሎት በተለይ የመክፈል አቅም የሌላቸው ሰዎችን ለመደገፍ የጎላ ሚና አለው” ብለዋል።