በደቡብ ሱዳን በኩል 502 የድሽቃና የክላሽ ጥይቶች ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ ተያዙ

137
ጋምቤላ ጥቅምት 22/2011 በደቡብ ሱዳን በኩል 502 የድሽቃና የክላሽንኮቭ ጠመንጃ ጥይቶች ወደ ሃገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ጋምቤላ ክልል ውስጥ መያዛቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ። በፌዴራል ፖሊስ የምዕራብ ዲቪዥን ሶስተኛ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ተረፈ በለጠ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ጥይቶች የተያዙት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ አማካኝነት ጥቅምት 18 እና 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው። ከተያዙት ጥይቶች መካከልም 79ኙ የዲሽቃ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የክላሽንኮቭ መሆናቸውን የገለጹት ኢንስፔክተሩ በድርጊቱ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችም ተይዘው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ የደቡብ ሱዳን አዋሳኝ የድንበር ኬላ በኩል የድሽቃ ጥይቶችን በባጃጅ ጭነው ወደ ላሬ ወረዳ ለማስገባት ሲሞክሩ የተያዙ ሲሆን የክላሽንኮቭ ጥይቶቹ ደግሞ በአንድ ግለሰብ ቤት መገኘታቸውን ተናግረዋል። ቀሪ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በሁለቱ ግለሰቦች ላይ የሚደረገው ምርመራ እንደተጠናቀቀ ክስ የሚመሰረት መሆኑን አስረድተዋል። በክልሉ በኩል የጦር መሳሪያዎች ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡበት እድል እንዳለ የገለጹት ኢንስፔክተር ተረፈ ይሔን ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ለሚያደርገው ክትትል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም