በጥበበ ህይወት የሰው ሃይል ለማፍራት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በቀጣዩ ዓመት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ይደረጋል

1297

ቢሾፍቱ ጥቅምት 22/2011 በኢትዮጵያ በጥበበ ህይወት (ባዮ ቴክኖሎጂ) የሰው ሃይል ለማፍራት የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሊተገበር ነው።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት የተዘጋጀው የጥበበ ህይወት(ባዮ ቴክኖሎጂ) ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት ባለድርሻ አካላት ጋር ፍኖተ ካርታውን የተመለከት ውይይት በቢሾፍቱ እየተካሄደ ይገኛል።

ፍኖተ ካርታው በዋናነት በጤና፣ግብርና፣በአካባቢና ኢንዱስትሪ የጥበበ ህይወት ዘርፎች የሰው ሃይል ለማፍራት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ዘሪሁን ከበደ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት አግባብነት፣ጥራት፣ፍትሐዊና ውጤታማ የምርምር ቴክኖሎጂ ስርጸትና ስርአት ትምህርት መገንባት ያስፈልጋል።

አዲሱ የጥበበ ህይወት ፍኖተ ካርታ ገበያው ከገበያው ጋር የተጣጣመውን የሰው ሃይል ለማፍራት ተግባራዊና ችግር ፈቺ ምርምር ለማድረግ ለማስቻል እንደሆነ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ በበኩላቸው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የስረአተ ትምህርት ገበያው ከሚፈልገው አንጻር ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራት የሚያስችል እንዳልነበረ አውስተዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው የጥበበ ህይወት ፍኖተ ካርታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸው የሚያወጡትና ያልተቀናጀና ወጥነት የሌለው ነበርም ብለዋል።

በተጨማሪም ፍኖተ ካርታው ከቅድመ እስከ ድህረ ምረቃ ያለው የጥበበ ህይወት ስርዓተ ትምህርት የትምህርት ግብአት ያልተሟላና በተግባር ያልተደራጀ እንደሆነም አንስተዋል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እና የጥበበ ህይወትን ለማዘመን ሰፊ የባዮ ሳይንስ እውቀት ያለው የሰው ሃይል ማፍራት ያስፈልጋል ነው ያሉት ዶክተር ካሳሁን።

በዚህም አኒስቲትዩቱ በጥበበ ህይወት ያለውን የትምህርት ስርአት ክፍተት ለመፍታት ውጤታማና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ለማፍራት የ10 ዓመት የፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው ከቅድመ እስከ ድህረ ምረቃ ባሉ መርሃግብሮች ለመማርና ማስተማር ስርአቱ የሚያገለግሉ የማስተማሪያ መሳሪያዎች የተዘጋጁለት መሆኑንና ፍኖተ ካርታውን ለማዘጋጀት ከተለያዩ አገራት ተሞክሮ መወሰዱን አመልክተዋል።

ውይይቱ እስከ ነገ የሚቀጥል ሲሆን በፍኖተ ካርታው ላይ መካተት ያለባቸውን ተጨማሪ ምክረ ሀሳቦች በባለድርሻ አካላት እንደሚነሳ ይጠበቃል።

ፍኖተ ካርታው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ አኒስቲዩትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅንጅት ፍኖተ ካርታውን ተግባራዊ ያደርጋሉ።