አሰራርን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይል ላይ መስራት ይገባል-የአዲስ አበባ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን

68
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 አሰራርን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይል ላይ መስራት ይገባል ሲል የአዲስ አበባ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገለጸ። ባለስልጣኑ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ለተቀላጠፈና ዘመናዊ አሰራር የሰው ኃይል አስፈላጊ ስለሆነ፣ አደረጃጀቱንና አሰራሩን ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል። የአዲስ አበባ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሞደርናይዜሽንና ኮርፖሬት ዘርፍ  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስመኘው ተሾመ በዚሁ ወቅት አንደገለጹት፣ ለግብር  ከፋዩ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሰራተኞችን ብቃት በየጊዜው ማሳደግ ይገባል ። በመሆኑም በገቢ ግብር አዋጅ፣ በታክስ አስተዳደር አዋጅ ፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅና በሌሎችም አዋጆች ላይ ስልጠናዎች ተሰጥቷል ብለዋል። የዚህ ስልጠና ዋና አስፈላጊነትም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣትና የሰው ኃይልን ለማጠናከር ሲሆን ስልጠናውም ባሉት 14 ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችና በዋናው መስሪያ ቤት ለሚገኙት ከ250 በላይ ለሆኑት አመራሮች እንደተሰጠ ገልጸዋል። የሰው ኃይል ላይ ካልተሰራ ሌሎችን ለውጦች ማየት የማይታሰብ በመሆኑም ከመጪው ህዳር ጀምሮ ለመስሪያ ቤቱ ሰራተኞችም ተመሳሳይ ስለጠናዎች ለመስጠት እንደታቀደም ተገልጿል። ባለ ስልጣኑ በ2010 ዓ.ም የስነምግባር ችግር የነበረባቸውን 18 ሰራተኞች ያሰናበተ ሲሆን 117 የሚሆኑ ከባድና ቀላል የተለያዩ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውን ሰራቶኞቹን የተለያየ የእርምት እርምጃዎች እየወሰደባቸው አንደሆነም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። በ2011ዓ.ም የሶስት ወራት 1 ማሰናበቱን፣ ለ11 ከባድና ለ4 ቀላል ስነምግባር ችግር ለታየባቸው ሰራተኞች የእርምት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል። የግብር ከፋዩን የአገልግሎት አሰራር ለማሻሻል በተያዘው እቅድ መሰረትም ችግር ያለባቸውን ሰራተኞች በመለየት እርምጃ መወሰዱ የታሰበውን ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራር ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል። የመረጃ ቴክኖሎጂ ከማዘመን አንጻረም እየተሰራበት እንዳለ አቶ  ስመኘው ገልጸው፣ ግብር ከፋዩ ሳይቸገር አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል አሰራሩ መዘመን ተገቢነት እንዳለው ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት የግብር ከፋዮች አመለካከት የተቀየረና የሚመሰገን ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል የሚያሳዩትን ፍላጎት ይበልጥ ለማሻሻል መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል። 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጥቅምት ወር ግብር ለመሰብሰብ ብር  ከታቀደው  1.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት የግብር ከፋዮች ሁል ጊዜም እንደ ልማድ በመውሰድ ግብርን ወደ መጨረሻ ስለሚከፍሉ እንደሆነም ተጠቁሟል። ይህ አይነቱ አሰራር በጥቂት ጊዜና የሰው ኃይል ለመስራት አስቸጋሪ ስለሚሆን ተገልጋዮች በጊዜ የመክፈል ባህል ሊያዳብሩ እንደሚገባም ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እራሱን ችሎ የተቋቋመው በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም ነበር።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም