ባለፉት ሁለት ወራት ከ6 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የእምቦጭ አረም ማስወገድ ተቻለ

43
ጎንደር ግንቦት 14/2010 በጣና ሐይቅ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ሥራ የጀመረውን የአረም ማስወገጃ ማሽን በመጠቀም ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ6 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ አረም ከሐይቁ ለማስወገድ መቻሉ ተገለጸ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሕብረተሰቡ የጉልበት ተሳትፎ በአረሙ ተወሮ የነበረ ከ4ሺህ ሄክታር በላይ የሐይቁ አካል ከአረሙ ነጻ ማድረግ መቻሉም ተመልክቷል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም መምሪያ የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ሙሉ ስሉጥ ለኢዜአ እንደተናገሩት ማሽኑ በአሁኑ ወቅት በተሟላ መንገድ አረም የማስወገድ ሥራ በማከናወን ላይ ነው፡፡ በአማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር 2 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ተገዝቶ ሥራ የጀመረው ዘመናዊ የአረም ማስወገጃ ማሽን አረም የማስወገድ ስራ እየሰራ ያለው በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ለምባ በተባለው የሐይቁ አካባቢ ነው፡፡ እስካሁንም ማሽኑ 6ሺህ 260 ሜትር ኪዩብ አረም ማስወገዱን የተናገሩት ቡድን መሪው፣ ተጨማሪ ማሽኖችንም በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የተጠናከረ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ ክልሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ በተጀመረው የህዝብ ንቅናቄም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 174ሺህ ህዝብ የተሳተፈበት የእምቦጭ አረም ማስወገድ ዘመቻ በሐይቁ አዋሳኝ በሆኑ ጎንደር ዙሪያ፣ ምዕራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች ተካሂዷል። በወረዳዎቹ በሚገኙ 16 ቀበሌዎች ሕብረተሰቡ ባደረገው የጉልበት አስተዋጽኦ 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአረም ማስወገድ ሥራ በሐይቁ ላይ ለማከናወን ተችሏል፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ ሀይቁን ወሮ የነበረውን 4ሺህ ሄክታር የሸፈነ የእምቦጭ አረም ከሐይቁ ላይ ማስወገዱን ቡድን መሪው አስታውቀዋል፡፡ በጋ ላይ ብቻ ሲካሄድ የቆየውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ ሥራ በክረምትም ማካሄድ እንዲቻል ለምባ በተባለው የሐይቁ አካባቢ ሁለገብ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል የወደብ ግንባታ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ "በተጨማሪም ክረምት ከበጋ ወደ ሐይቁ የሚያስገባ የ7 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ በክልሉ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ሥራው ተጀምሮ በመፋጠን ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡ "የክልሉ መንግስት በዘንድሮ አመት አረሙን ለማስወገድ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለህብረተሰቡ አጋዥ የሆነ የአረም ማስወገጃ ማሽን ማስገባቱ አስደስቶናል" ያሉት ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አርሶአደር ታከለ አየነው በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት ሕብረተሰቡ ሐይቁን ከእቦጭ ለመታደግና አረሙን ለማጥፋት በጉልበቱ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ "በየአመቱ በሰው ጉልበት የምናደርገው አረም የማስወገድ ሥራ ከአረሙ መልሶ በፍጥነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተስፋ ቆርጠን ነበር "ያሉት ደግሞ ሌላው አርሶአደር ማሩ ቸሬ ናቸው፡፡ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አዝማች ብርሃኑ የአረም ማስወገጃ ማሸኑ ሥራ መጀመር በሕብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃት ከመፍጠሩም በላይ የህብረተሰቡን ድካም በመቀነስ በኩል እገዛው የላቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የክልሉ የቅርብ ጊዜ የጥናት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት የእምቦጭ አረም ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ የጣና ሐይቅን ወሮ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም