አቶ ሰለሞን አረዳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኑ

131
አዲስ አበባ ጥቅምት 22/2011 አቶ ሰለሞን አረዳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምከትል ፕሬዝዳንት በመሆን ተሾሙ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ አራተኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ሲካሄድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሹመትን አጽድቋል። አቶ ሰለሞን አረዳ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ፍርድ ቤቱን በፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ ከቆዩት አቶ ጸጋዬ አስማማው በመረከብ ነው። አቶ ሰለሞን በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ህግ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በህዝብ አስተዳደር ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ፤ እንዲሁም ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ በህግ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። የስራ ዝግጅታቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለረጅም ጊዜ በዳኝነት ያገለገሉ፣ በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በዳኝነትና በምክትል ፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ፣ ለአገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች የማማከር አገልግሎት የሚሰጡ፣በአፍሪካ በህግ ባለሙያነታቸው የሚያገለግሉ ናቸው። በኔዘርላንድስ ሄግ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት በ "ፐርማነንት ኮርት ኦፍ አርብትሬሽን" በመስራት ላይ የሚገኙና ባለፉት 21 ዓመታት በመስኩ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሹመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም