በኮምቦልቻ ከተማ በተከሰተ የውሃ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ለችግር ተዳርገናል....የከተማዋ ነዋሪዎች

49
ደሴ ግንቦት 14/2010 በኮምቦልቻ ከተማ በተከሰተ የውሃ አቅርቦት እጥረት ምክንያት ለከፍተኛ ወጭ መዳረጋቸውን አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ የከተማዋ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው በማሽን ብልሽት ምክንያት መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኮምቦልቻ ከተማ አሰብ በር አካባቢ ነዋሪ የሆነችው ወጣት እመቤት ሽባባው ለኢዜአ እንደገለጸችው የውሃ እጥረት ከገጠማቸው ከሳምንት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት  አንድ ጀሪካን ውሃ ከሌላ አካባቢ በሰው ሸክም ለማስመጣት እስከ 10 ብር ድረስ እያወጡ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ "ውሃ የሚመጣው በሌሊት በመሆኑ ውሃ ወዳለበት ቦታ ስንሄድ ለደህንነት ስጋት እየተጋልጥን ነው" ብላለች፡፡ በከተማዋ ቀበሌ 03 ነዋሪ አቶ የሱፍ ቃሲም በበኩላቸው በተለይ ወቅቱ የረመዳን ጾም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በውሃ እጥረቱ እንደተቸገሩ ገልጸዋል፡፡ በቀን ከአምሳ ብር በላይ ለውሃ ብቻ እንደሚያወጡ የተናገሩት አቶ የሱፍ፣ ይህም ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የንጹህ መጥጥ ውሃ እጥረቱ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ውስጥም መከሰቱንና ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደገሞ የኮሌጁ የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ቡድን አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ዳውድ ናቸው፡፡ በተለይም ለተማሪዎች የጽዳት አገልግሎት ከደሴና ከሀርቡ ከተሞች ውሃ በቦቴ በማመላለስ የማከፋፈል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የኮሌጁ አስተዳደር ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረትም እያንዳንዱ ተማሪ ከትናንት ጀምሮ በቀን ሁለት ሊትር የታሸገ ውሃ እንዲያገኝ በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በኮሌጁ የጨርቃ ጨርቅ ትምህርት ክፍል የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ኑርባንተ መንበር በበኩሉ የውሃ እጥረቱ ቢከሰትም የኮሌጁ አመራሮች ለተማሪው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ላደረጉት ጥረት አድናቆቱን ገልጿል፡፡ የአምስተኛ ዓመት የሲቪል ምህንድስና ተማሪ የሆነው ሃብታሙ መኮንንም በተመሳሳይ ሁኔታ የውሃ ችግር እንደነበር ጠቁሞ፣ ኮሌጁ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የታሸገ ውሃ ለመጠጥነት እያገኙ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፉ ተዘራ በበኩላቸው ችግሩ የተከሰተው ውሃውን ወደ ጋን ገፍቶ ለተጠቃሚዎች እንዲዳረስ የሚያደርገው ማሽን በመበላሸቱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማሽኑ ከተበላሸ 15 ቀናት  እንደሆነው የገለጹት አቶ ተስፉ በዚህም ምክንያት ጽህፈት ቤቱ በከተማዋ ለሚገኙ ደምበኞቹ ውሃ በፈረቃ ለማዳረስ መገደዱን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ማሽኑ ከመበላሸቱ በፊት በቀን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር በላይ ውሃ ለተጠቃሚዎች ይከፋፈል ነበር፡፡ በአሁን ወቅት ግን በቀን እየተሰራጨ ያለው 500 ሺህ ሊትር ውሃ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከተጠቃሚው ፍላጎት ጋር እንደማይጣጣም አምነው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአማራ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ጋር በተደረገ ስምምነት ተጨማሪ ማሽኖችን ለማስመጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስረድተዋል። ማሽኖቹን እስከ ሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ድረስ አስመጥቶ በመትከል ነባሩን አገልግሎት ለመስጠት ርብረበ እንደሚደረግ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም