የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ለመስራት ስምምነት አደረገ

1630

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

በመዲናዋ በሚካሄዱ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በቅንጅት በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂደዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተስፋፋ የመጣውን የከተሜነት ዕድገት በኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎችን በፍጥነት መስራት ያስፈልጋል።

ከተማዋ በቤት ልማት፣ በመሰረተ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎች መስኮች ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት በመላው አገሪቱ ላሉት 2 ሺህ ከተሞች ዕድገት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

እስከ አሁን ባለው ሂደት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ሙያዊና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት በኩል የክህሎት ክፍተት መኖሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ችግሩን ለማስወገድ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

በተጨማሪም የተሟላና በቂ የአቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት በኩል ሚኒስቴሩ ያሉበትን ውሱንነቶች ለማስወገድ የውጭ አገር ተሞክሮን በመቀመር የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አማካሪ ወይዘሮ መስከረም ታምራት በበኩላቸው በአስተዳደሩ በኩል የተቀናጀና የተናበበ የጋራ ዕቅድ በማቅረብ በኩል ክፍተቶች እንዳሉ ገልጸዋል።

በመሰረተ ልማት ዘርፍ የሚታዩ ማነቆ አሰራሮችን በመቀየር ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል።

አስቸኳይ ውሳኔ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዩች ላይ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በኩል አስተዳደሩ በትኩረት የሚሰራበት ጉዳይ እንደሆነም ገልጸዋል።