በአዲስ አበባ የውሻ ባለቤት ለመሆን ህጋዊ የእውቅና ምስክር ወረቀት መያዝ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ ይደረጋል

86
አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የውሻ ባለቤት ለመሆን ህጋዊ የእውቅና ምስክር ወረቀት መያዝ የሚያስገድድ ህግ ተግባራዊ እንደሚደረግ የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። በከተማዋ ባለቤት አልባ ውሻዎችን በዘመቻ የማስወገድ ሥራ እንደሚከናወንም ተገልጿል። የከተማው ነዋሪዎች የውሻ ባለቤት ለመሆን ህጋዊ እውቅና ምስክር ወረቀት የመያዝ ግዴታ የሚጥል የህግ ድንጋጌ እንደሚተገበርም ተጠቁሟል። በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የከተማ ግብርና ዘርፍ የእብድ ውሻ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተግባራዊ የሚያደርገው ደንብና መመርያ ይፋ አድርጓል። በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የከተማ ግብርና ዘርፍ ሓላፊ አቶ አሰግደው ኃይሌጄወርግስ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የባለቤት አልባ ውሻ ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የሚያስከትለውም ጉዳት እየጨመረ መጥቷል። ይሄን አደጋ ለመከላከልና በዜጎች የሚደርሰው ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ደንብና መመርያ ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ላይ መደረሱን አመልክተዋል። ''በ2006 ዓ.ም የቁጥጥር ደንብ ቢወጣም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ችግርና የማስፈፀሚያ መመሪያ ባለመውጣቱ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል'' ያሉት አቶ አሰግደው በአሁኑ ወቅት መመሪያ ወጥቶ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ጠቁመዋል። ተግባራዊ የሚደረገው ደንብና መመሪያ ማንኛውም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ውሻውን አስመዝግቦ ምስክር ወረቀት ሳይዝ ባለቤት መሆን እንደማይችል ደንግጓል። በወረዳ ንግድ ፅህፈት ቤቶች ውሾች የሚመዘገቡበት መዝገብ መዘጋጀቱን የገለፁት አቶ አሰግደው መረጃው በዳታ ቤዝ እንደሚያዝ ተናግረዋል። ''ማነኛውም ሰው ውሻ ማስመዝገብ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን የውሻ ባለቤት አድራሻ ሲቀይርም የውሻው አድራሻም አብሮ መቀየር ይጠበቅበታል ነው'' ያሉት። የትኛውም የውሻ ባለቤት በደንቡና መመሪያው መሰረት የባለቤትነትና የክትባት ምስክር ወረቀት ካላሟላ ከ1 ሺህ እስከ 2ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ገልጸዋል። የውሻ ባለቤቶች በዓመት አንድ ጊዜ የማስከተብ፣ የውሻው ጤና በይዞታ ሥር የመንከባከብና ሲሞትም እንዲቀበር ለመዘገበው የወረዳ ንግድ ፅህፈት ቤት የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ተናግረዋል። አዲስ አበባ ባለቤት አልባ ውሻዎችን የማስወገድ ሥራ ለማከናወንም የሚያስፈልግ መድሀኒት ወደ ሁሉም ክፍለ ከተሞች መሰራጨቱንም አቶ አሰግደው አመልክተዋል። በ2010 በጀት ዓመት ከ13 ሺህ በላይ ባለቤት አልባ ውሻ መወገዳቸውን የታወቀ ሲሆን ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻም 1ሺህ433 ውሾች መወገዳቸውን ለማወቅ ተችሏል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም