ለአካባቢያቸው ሰላም የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ በነቀምቴ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ

50
ነቀምቴ አዲስ አበባ 20/2011 በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ በነቀምቴ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። ከከተማዋ የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ በነቀምት ከተማ መክረዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ተሾመ ገመዳ እንዳሉት ሰላምን በተናጥል ማረጋገጥ አስቸጋሪ ስለሚሆን ሁሉም ወገን በአንድነት ሊቆም ይገባል። በተለይ ማንም ሰው በዘፈቀደ ተነስቶ ማህብራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትንና መንገድ የሚዘጋበት ሁኔታ ህገወጥ በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና ስርዓት አልበኝነት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ሁኔታ በእዚህ ከቀጠለ የከተማዋን ዕድገት የሚገታ በመሆኑ ለሰላም ማስፈን ይመለከተኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ከዚህ ዓይነቱ ድርጊት ራሱን እንዲቆጠብ አሳስበዋል። አባገዳ አያና ቃበታ በበኩላቸው ጸረ ሠላምና ልማት የሆኑ ኃይሎችን ሴራ ማክሸፍ የሚቻለው ሁሉም በዘር፣ በሃይማኖትና በጾታ ልዩነት ሳይፈጥር አንድነቱን በማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ቄሮዎች በበኩላቸው ጊዜው እርስ በርስ በመከፋፈል የሚዋጉበት፣ መንገድ የሚዘጋበት፣ በከተማና በገጠር ልዩነት ተፈጥሮ ግጭት ውስጥ የሚገባበት ሳይሆን ለኦሮሞ አንድነት በጋራ የሚሰራበት መሆኑን ተናግረዋል። ቄሮ ከምንጊዜውም በላይ ለሠላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ መስፈን ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለበትም ተናግረዋል። የነቀምት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቦጋለ ሹማ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ችግር እየተፈጠረ ያለው በስሜት በሚነሳሱና በቄሮ ስም በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንን ሁኔታ ለመከላከልና የከተማዋን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ እውቅና ያላቸው ቄሮዎች ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አሳስበዋል። "በአሁኑ ወቅት በከተማውና በተለያዩ የክልሉ ዞኖች በቄሮ ስም እየተደረገ ያለው አሉታዊ እንቅቃሴ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ወደኋላ የሚመልስ እንጂ ምንም ዓይነት ፋይዳ የለውም" ብለዋል። ቄሮዎችና ሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ላመጡት ለውጥ እውቅና እንደሚሰጡ የገለጹት ከንቲባው አሁን በአገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ከሁሉም አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም