በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከሱዳኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

1610

አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በቅርቡ የሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙት ኦስማን መሐመድ ዩሱፍ ኪብር ጋር በሁለትዮሽ ትብብር ላይ ተወያዩ።

አምባሳደር ሽፈራው በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ጠንካራ መሆኑን ገልጸው በዘርፉ ያለውን ትብብር ከዚህ በላይ ማሳደግ የሚያስችል አቅም በመኖሩ ትኩረት ተደርጎ እተሰራበት መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሁለቱን አገሮች በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማሳለጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተም በሱዳን በኩል ያለው በመርህ ላይ የተመሰረተ አቋም የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ኦስማን መሐመድ የሱፍ ኪብር በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረሙ እንደ ንግድ፣ የመሰረተ-ልማት ትስስርና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንዲተገበሩ በጋራ እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል።

የህዝብ ለህዝብ ትብብሩን ለማጠናከርና ለችግሮች መፍትሄ ለመስጠት በሁለቱም ወገን በትኩረት እየተሰራበት በመሆኑ ከድንበር ጋር በተያያዘም ምንም ዓይነት ግጭት እንደማይኖር ተናግረዋል።

የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተም የሱዳን አቋም ግልፅ መሆኑን ጠቁመው ግድቡ ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች የሚጠቅም በመሆኑ ሱዳን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ምክትል ፕሬዚዳቱ ሁለቱን አገሮች በመንገድ፣ በባቡር፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች በተቻለ ፍጥነት ለማስተሳሰር ተጀመረውን ጥረት መንግስታቸው አጠናክሮ እንደሚቀጠልበትም መግለጻቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።