የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

80
ደብረ ብርሃን ግንቦት 14/2010 የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ከአፋርና ኦሮሚያ ክልል ከተውጣጡ የትምህርት ባለሙያዎች ጋር በትምህርት ጥራት ዙሪያ በደብረ ብርሃን ከተማ እየመከረ ነው። በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ስልጠና ጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት የኢንሰፔክሽን ባለሙያ ወይዘሮ ገነት በላይነህ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ባለሙያዎችን በስልጠና በማብቃትና ፖኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው። በተለይም በመማር ማስተማር፣ የትምህርት ቤት አመራሮችን በማብቃት፣ ምቹ የትምህርት ቤት ሁኔታና አካባቢ በመፍጠር እንዲሁም የህብረተሰቡን ተሳትፎ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የምክክር መድረኩ በትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ መርሃ ግብሩ አተገባበር ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ስልጠናና ጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ በቃሉ መላኩ በበኩላቸው አሁን ላለው የትምህርት ጥራት መጓደል እንዲህ አይነት የውይይት መድረኮች  ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ የሚገኙ ግብዓቶች ወደ ተግባር በመቀየር ከችግሩ ለመውጣት የትምህርት ባለሙያውና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ይገባል ያሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ትምህርት መምሪያ አጠቃላይ የኢንስፔክሽን ትምህርት ባለሙያ አቶ አለሙ ደምሴ ናቸው። በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት ኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ነጋሽ በበኩላቸው  በትምህርት  ተደራሽነት ላይ የተገኘው ውጤት ወደ ጥራት ለመቀየር ከፌደራል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ቅንጅታዊ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ ትናንት በተጀመረውና ለአምስት ቀናት በሚካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ከአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች የተውጣጡ 75 የትምህርት ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም