በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት መዝገብ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ

58
አዲስ አበባ ጥቅምት 19/2011 በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ መሐመድ ዑመር መዝገብ የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች ላይ የ10 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ። ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በጅግጅጋና አካባቢዋ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንትና የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ፈራሃን ጣሄር ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ነበር። መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ የተለያዩ የምርመራ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጾ፤ ተጨማሪ ግብረ አበሮችን ለመያዝ፣ ከመቃብር የወጣ አስክሬን ምርመራ ውጤትን ለማምጣት፣ የቴክኒክ ምርመራ ውጤቶችን መቀበል፣ በብጥብጡ የተደፈሩ ሴቶችና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ከተለያዩ ሆስፒታሎች የሕክምና ማስረጃ የማሰባሰብ ስራዎች እንደሚቀሩት አስረድቷል። ለብጥብጥ ሲያገለግሉ የነበሩ የጦር መሳረዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃዎች ከሶማሊኛና ከእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ወደ አማርኛ ቋንቋ የማስተርጎም ስራዎች እንደሚቀሩትም ገልጿል። በመሆኑም ቀሪ ስራዎቹን ለማከናንም የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል። የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው "ፖሊስ ለተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም፤ ከዚህ በፊት በነበሩት ቀጠሮዎች በተመሳሳይ ቋንቋ የተገለጹ አንድ አይነት ምክንያች ናቸው" ሲሉ ተከራክረዋል። በዚህም ተጠርጣሪዎች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸው እንዲከበር ጠይቀው፤ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ እንዳይፈቀድ፣ ከተፈቀደም ከአምስት ቀናት እንዳይበልጥ አመልክተዋል። ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩና የወንጀል ድርጊቱ ሂጎ የተባለ ህገ-ወጥ ቡድን ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር በመሆን በዘር፣ በኃይማኖትና ቋንቋ ላይ የተፈጸመ ውስብስብ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቃል ብሏል። ክልሉ ሰፊ፣ ጠረፋማና በርሃማ በመሆኑ ተጨማሪ ግብረ አበሮችን ለመያዝና አስፈላጊውን ምርመራ ለማድረግ ጊዜ ይጠይቃልም ብሏል ፖሊስ። ግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱ የወንጀል ድርጊቱን መወሳሰብና ክብደት ከግምት ውስጥ ማስገባት መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ 10 ቀናትን ፈቅዷል። በዚህም በተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው በሶስት መዝገብ ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የፖሊስን ምርመራ ውጤት ለመስማት ለጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም