ኢትዮጵያና ሳዑዲ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

54
ሪያድ ጥቅምት 18/2011 ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ በኢንቨስትመንት፣ በኃይል ማመንጫ ልማት እና አጠቃላይ የቢዝነስ ትብብር ላይ ውይይት አካሄዱ። በውይይቱም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል እና በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ አብዱልአዚዝ አሕመድ ተገኝተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ኢኒሼቲቭ ስብሰባ ተካፋይና የፓናል ውይይቱ አካል እንድትሆን በሳዑዲ ንጉስ መመረጧ እንዳስደሰታቸው ለአገሪቱ የኢንቨስትመንት ኃላፊ ኢብራሂም አል-ኡመር ገልጸውላቸዋል። ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተካፋይ መሆኗ ያላትን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታና አማራጮች ለሳዑዲ አረቢያና ለዓለም አቀፍ ባለሃብቶች እንድታስተዋውቅ ይረዳታል ብለዋል። የሳዑዲ አረቢያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፎች በግብርና እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ቢሳተፉ ጥቅሙ ለሁለቱም ወገኖች የጎላ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት ጠቁመዋል። ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ በአዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን እና ሁለቱም አገራት በአካባቢያቸው ትልልቅ ሚና እንደሚጫወቱ እንዲሁም ትልልቅ ስራቴጂያዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። የሳዑዲ አረቢያው የኢንቨስትመንት ኃላፊ ኢብራሂም አል-ኡመር በበኩላቸው ዓለም አዲሷን ኢትዮጵያ እየተመለከተ መሆኑንና አዲሱ የመንግስት አስተዳደር ቁርጠኛ አመራር፣ ግልፅና የጠራ ራዕይና ግብ ያለው ነው ሲሉ ገልጸዋል። በመሆኑም ንጉስ ሰልማን ቢን አብዱልአዚዝ እና አልጋወራሽ ሙሀመድ ቢን ሰልማን ከዚህ የኢትዮጵያ አመራር ጋር ያላቸውን የኢንቨስትመንት ትሥሥር ማጠናከር እንደሚፈልጉ አክለዋል። አክዋ ፓወር የሚባለው የሳዑዲ አረቢያ የታዳሽ ኃይል አመንጪና አቅራቢ ድርጅት በኃይል ማመንጨትና አቅርቦት ላይ በኢትዮጵያ መሳተፍ እንደሚፈልግም ኢብራሂም አል-ኡመር ገልፀዋል። የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደሚያበረታታ ገልፀው፣ በባለሃብቱ በኩልም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ትልቅ ፍላጎትና ግፊት እንዳለ ተናግረዋል። በሁለት ሳምንታት ውስጥ የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ አሳውቀው፤ በኢትዮጵያ በኩል ቅድመ ዝግጅት በማድረግና ኢንቨስትመንት ፎረም በማዘጋጀት የቢዝነስ አማራጮችንና እድሎችን ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝታቸው ከአልጋወራሽ ልዑል ሙሃመድ ቢን ሰልማን ጋር የነበራቸው ምክክር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሻሻል ወሳኝ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም